ቀጥታ፡

በዞኑ ፍራፍሬን በኩታ ገጠም በማልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው

ጎንደር ፤ ሐምሌ 13/2018(ኢዜአ)፦በማእከላዊ ጎንደር ዞን ፍራፍሬን በኩታ ገጠም በማልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ንጉሴ ማለደ ገለጹ። 

በዞኑ በላይ አርማጭሆ ወረዳ በሹመራ ቀበሌ የቡናና አቮካዶ ፍራፍሬን በኩታ ገጠም ለማልማት የሚያስችል የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ዛሬ ተካሂዷል። 


 

የዞኑ ግብርና  መምሪያ ኃላፊ አቶ ንጉሴ ማለደ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በዞኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የተሰጠው ትኩረት  አበረታች ውጤት ለማስመዝገብ  አስችሏል። 

ባለፉት ዓመታት በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር 4 ሺህ 900 ሔክታር መሬት በቡና በማልማት  የአርሶ አደሩን  ኢኮኖሚያዊ  ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስችሏል ነው ያሉት። 

በያዝነው ክረምትም በ500 ሄክታር መሬት ላይ የቡና ችግኝ እንደሚተከል ጠቁመው ከዚህ ውስጥ 100 ሄክታር የሚሆነው በላይ አርማጭሆ ወረዳ በኩታ ገጠም የሚለማ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም አርሶ አደሩን ከሰብል ልማቱ ጎን ለጎን በፍራፍሬ ልማት በማሳተፍ በዘላቂነት ሀብት ለማፍራት  የሚያስችለው መሆኑን አስገንዝበዋል።


 

በዞኑ የላይ አርማጭሆ ወረዳ የሹመራ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ባንቺ ደመቀ ፤ ቀደም ሲል ከተከሉት የቡና ችግኝ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ይህንኑ ተግባር በማጠናከርም ዘንድሮ በኩታ ገጠም የቡና ችግኝ  ተከላ መጀመራቸውን  ነው የተናገሩት።

በቡና ክላስተር ልማት እየተሳተፉ የሚገኙት አርሶ አደር ወርቁ ተፈራ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል የማንጎ ችግኞችን በማልማት ተጨማሪ ሃብት ለመፍጠር እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።


 

አሁን ላይም ቡናን በኩታ ገጠም ለማልማት ከአጎራባች አርሶ አደሮች ጋር በመተባበር እየሰሩ መሆናቸውን አስገንዝበዋል። 

የፍራፍሬ ችግኞቹንም  በማረም፣ በመኮትኮትና በመጠበቅ ለፍሬ ለማብቃት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 

በዞኑ በክረምት አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 141 ሚሊዮን የደን፣ የፍራፍሬና የውበት ችግኞችን የመትከል ስራ መቀጠሉን ከዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም