ኢትዮጵያ በልማት እንቅስቃሴዎችና በውጭ ግንኙነት መስክ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበች ትገኛለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በልማት እንቅስቃሴዎችና በውጭ ግንኙነት መስክ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበች ትገኛለች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በልማት እንቅስቃሴዎችና በውጭ ግንኙነት መስክ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች የሀገሪቱን ሁለተናዊ ብልፅግና ከማረጋገጥ ባለፈ የውሳኔ ሉዓላዊነትን በተግባር ያረጋገጡ መሆናቸውን ምሁራን ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር እንዳለ ንጉሤ እንደገለጹት፤ በፖለቲካ ሳይንስና ዲፕሎማሲ መስክ ሉዓላዊነት ሀገራት በውስጣዊም ሆነ በውጭ ጉዳዮቻቸው ላይ ያለማንም ጣልቃ ገብነት በነፃነት የመወሰን ሙሉ ባለቤትነትን ማረጋገጥ መቻል ነው።
ከለውጡ በኋላ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ማዕከል ያደረገ የዲፕሎማሲ አካሄድ እየተከተለች እንደምትገኝ ገልፀው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅና ወደ ሥራ ማስገባት የመወሰን ነጻነት የታየበት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሕጋዊና ሞራላዊ መሠረት ያለው የባህር በር የማግኘት ጥያቄን በማንሳት ለዓለም ማህበረሰብ የማስገንዘብ ተግባር እያከናወነች መሆኗም የውሳኔ ሉዓላዊነቷ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
በሀገር ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ሁለተናዊ ዕድገት ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ለአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች መጠናከር ያላቸውን ቁልፍ ሚና በግልጽ ያሳያሉ ብለዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዶክተር መብራቱ አለሙ በበኩላቸው የዲፕሎማሲ አቅም ከሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ጥንካሬ ጋር የተሳሰረ መሆኑን ገልፀዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግስት ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ መግባቱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የዕዳ ጫናና የዋጋ ንረት ችግሮችን መፍታት ማስቻሉን አንስተዋል።
የግል ዘርፉን በማጠናከር፣ የውጭ ባንኮችና ካፒታል ወደ ሀገር እንዲገቡ በር በመክፈትና የካፒታል ገበያን ስርዓትን በመዘርጋት የሀገሪቱን የፋይናንስ አቅም ማሳደጉን ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚም የኤክስፖርት መጠንን በማሳደግና በብድርና በእርዳታ ላይ ያለውን ጥገኝነት በመቀነስ የውሳኔ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
በከተሞች በኮሪደር ልማት እየተመዘገበ ያለው ፈጣን እድገት የሀገሪቱን ዓለምአቀፍ ገጽታና የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከልነት እያሳደገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ማዕከል ያደረገ ባለብዙ ዘርፍ ዲፕሎማሲና ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የመስጠት መርህን እየተከተለች መሆኗም ለዲፕሎማሲ ስኬቷ መሰረት መሆኑን ምሁራኑ ተናግረዋል።