ቀጥታ፡

በደብረ ብርሃን ከተማ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ተጠቃሚ አድርገውናል

ደብረብርሃን፤ ሐምሌ 13/2018(ኢዜአ)፦  በደብረ ብርሃን ከተማ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ዘላቂ ተጠቃሚነታችንን ያረጋገጡ ናቸው ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

ከደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ በለጡ አስፋው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በከተማዋ የልማት፣ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች በትኩረት መሰራታቸው ተጠቃሚ እንድንሆን አድርጎናል ብለዋል።

በተለይም ወንጀል ይፈፀምባቸው የነበሩ አካባቢዎችን በማልማት ውብ፣ ሳቢና ማራኪ የመዝናኛ ስፍራ እንዲሆን መደረጉ በተሻለ መንገድ ነዋሪውን ተጠቃሚ ለማድረግ ያስቻሉ ናቸው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም የከተማዋን አድገት በሚያፋጥኑ የልማት ስራዎች ላይ በጉልበት፣ በገንዘባቸው እና በእውቀታቸው በመሳተፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሠይድ ማሩ በበኩላቸው፤ በከተማው የተካሄዱ የመንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ለወጣቶችና ለሴቶች የሥራ ዕድልን የፈጠሩ ናቸው  ብለዋል።

የተገነቡ የመሰረተ ልማቶች የአገልግሎት ጊዜያቸው እንዲረዝም የአካባቢውን ማህበረሰብ በማስተባበር የመጠበቅና የመንከባከብ ስራ እየሰሩ መሆኑን ነው ያመለከቱት። 

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሽት በበኩላቸው  እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተከናወኑ የልማት ስራዎች ከተማዋን የኢንዱስትሪ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ማእከል እንድትሆን ያስቻሉ ናቸው።


 

በዚሁ ወቅት ሰላምን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ህብረተሰቡ የተሳተፈበት የ75 ኪሎ ሜትር የጠጠርና ሶስት ኪሎ ሜትር የኮብል ስቶን መንገዶች መገንባታቸውን አስረድተዋል።

በተለይም በከተማዋ የተገነባው የሶስት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ ደረጃውን የጠበቀ የእግረኛና የሳይክል መንገዶችን ጨምሮ የመዝናኛ እና የአረንጓዴ ስፍራዎችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የቴሌኮሙኒኬሽንና የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን አሟልቶ የተገነባ በመሆኑ ለከተማዋ እድገትና ለህዝቡ ተጠቃሚነት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ19 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን ጠቁመው በአዲሱ በጀት ዓመትም ከዚህ የላቀ ስራ ለመስራት በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ አመልክተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም