ቀጥታ፡

በክልሉ የወጣቶችን የፈጠራ ችሎታ ለሚያጎለብቱ ተግባራት ትኩረት ተሰጥቷል

ጅግጅጋ፤ ሐምሌ 13/2018(ኢዜአ)፦በሶማሌ ክልል የወጣቶችን የፈጠራ ችሎታና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን  የሚያጎለብቱ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ አስታወቁ።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ የክልሉን ኢኖቬሽን ማዕከል መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በክልሉ የወጣቶችን የፈጠራ ችሎታና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማጎልበት አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመንና የዲጂታል ኢኮኖሚን ለማሳለጥ ትኩረት ተሰጥቷል።

በዚህም የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው የክልሉ የኢኖቬሽን ማዕከልም በቴክኖሎጂ ብቁ የሆኑ ዜጎችን ለማፍራት እና በዘርፉ አቅማቸውን ለማጠናከር ዕድል  የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

መንግሥት ለቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ልማት የሰጠው ትኩረት አበረታች ለውጦች እያስመዘገበ መሆኑን ጠቁመው ይህንኑ ለማስፋት እየተሠራ ነው ሲሉ አክለዋል። በቀጣይም ማዕከሉን የማስፋት፣ በግብአትና፣ በሙያተኞች የማጠናከር ስራ  በትኩረት እንደሚከናወን አመላክተዋል።



የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ሃላፊ መሀመድ አሊ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ የወጣቶችን  የፈጠራ ችሎታና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅም የሚገነባና ክህሎታቸውን የሚያጎለብት መሆኑን ተናግረዋል።

ማእከሉ የ2030 የዲጂታል እቅድ ስትራቴጂን ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ጠቁመው ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ  የተቋቋመ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ማዕከሉ በድረገጽ ልማት፣ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በመረጃ ትንተና፣ ሳይበር ሴኩሪቲ፣ ዲጂታል ዲዛይን አገልግሎት በመሳሰሉት ስልጠና የሚሰጥበት መሆኑን ተናግረዋል።

ማዕከሉ በተጨማሪም አነስተኛ ንግዶችን የማልማትና የምርምር አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በስነ ስርአቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ ወጣቶች፣ የፈጠራ ባለሙያዎች፣ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም