ቀጥታ፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በልማትና በመልካም አስተዳደር ዘርፎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል

ገንዳ ውሃ፤ ሐምሌ 13/2018 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በልማትና በመልካም አስተዳደር ዘርፎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤታማ ተግባራትን ለማስመዝገብ መቻሉን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ። 

​የዞኑ አስተዳደር የተጠናቀቀው በጀት ዓመት የመንግስትና የፓርቲ ስራ አፈፃፀም ግምገማና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ አካሄዷል።


 

​የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ እያሱ ይላቅ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህዝቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ጥረት የተደረገበት  ነው።

በተለይም ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች፣ የትምህርትና የጤና ተደራሽነትን የማስፋፋት ተግባራት ተጨባጭ ውጤት የታየባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥም የተጠናቀቁ የመንገድ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፣ የጤና ተቋማት ግንባታና ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎችን ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

በአዲሱ በጀት ዓመትም የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝቡን ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ለመመለስ መላው አመራርና ህዝቡ በቁርጠኝነት ሊረባረቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

​በብልጽግና ፓርቲ የማእከላዊ ጎንደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እንዳለው ማሩ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡት ውጤቶች በአመራሩና በአባላቱ የተቀናጀ ጥረት የተገኙ ናቸው ብለዋል።


 

የተመዘገቡት ውጤቶች የመንግስት መዋቅሩ ፓርቲው በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሰረት መፈጸም በመቻሉ የመጣ ስኬት መሆኑን ጠቁመው ይህም በአዲሱ በጀት ዓመት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

​በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ያሉት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ጤናው ፋንታሁን ናቸው።


 

በዚህም በመኸርና በመስኖ ልማት ከ11 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ  ምርት ለማምረት መቻሉን አውስተዋል።

በአዲሱ በጀት ዓመትም የተጀመሩ የግብርና ምርትና ምርታማነት ማሳደጊያ ስራዎችና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል በተለየ ትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በመድረኩ የዞኑ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች  ተገኝተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም