በበጎ ፈቃድ አገልግሎት አቅመ ደካማ ወገኖችን በማገዝ ወጣቶች ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት አቅመ ደካማ ወገኖችን በማገዝ ወጣቶች ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው
ጊምቢ፤ ሐምሌ 13/2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ወለጋ ዞን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት አቅመ ደካማ ወገኖችን በማገዝ ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው ሲሉ የዞኑ ወጣቶች ገለጹ።
በምዕራብ ወለጋ ዞን በተያዘው ክረምት በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተግባራት ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል ወጣት አብዱረዛቅ አብዱልጀሊል፣ በክረምት ወቅት የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ የህሊና እርካታ ማግኘቱን ተናግሯል።
ወጣቱ አክሎም በአሁኑ ወቅት የአቅመ ደካሞች ቤት ዕድሳት ሥራ ላይ በመሳተፍ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ሌላኛው ወጣት ቢላል ሙሳ እንዳለው በደም ልገሳና በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ በየዓመቱ እንደሚሳተፍ አስታውሷል።
አገልግሎቱ የመረዳዳትና የመታጋገዝ ባህልን ከማጠናከር ባሻገር ወጣቶች የተለያዩ ልምዶችን በማግኘት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ሌላኛው ወጣት አማኑኤል ቀልቤሳ በበኩሉ በተያዘው የክረምት ወቅት በአካባቢ ጥበቃ፣ በአረንጓዴ አሻራና ሌሎች የልማት ዘርፎች ላይ እየተሳተፈ እንደሚገኝ ተናግሯል።
በተለይም በደም እጥረት ምክንያት የወገኖችን ሕይወት ለመታደግ በየሦስት ወሩ ደም እየለገሰ እንደሚገኝ ገልጿል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን በየዓመቱ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ የበኩሏን ድርሻ እየተወጣች እንደምትገኝ የተናገረችው ደግሞ ወጣት ሲንድቢን ግርማ ናት፡፡
በአገልግሎቱ የመተጋገዝ እና የመረዳዳት ባህላችን በመጠናከሩ ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖችን ችግር ለመቅረፍ እንደሚሠሩ ወጣቷ ተናግራለች፡፡
በምዕራብ ወለጋ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የወጣቶች አደረጃጀት እና ክትትል ድጋፍ ቡድን መሪ አቶ ተመስገን ታደሰ እንደተናገሩት፤ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጊዜና ጉልበታቸውን በልማት ሥራዎች ላይ በማዋል የበርካታ ወገኖችን ችግር እያቃለሉ ይገኛሉ።
በዘንድሮው የክረምት ወራት በዞኑ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ወጣቶች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በ42 የተለያዩ የልማት ዘርፎች ላይ በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመዋል።
በክረምት ወራቱ የአቅመ-ደካሞች ቤት ግንባታና ዕድሳት፣ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ የደም ልገሳ እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች በበጎ ፈቃድ መልክ ይከናወናሉ ብለዋል።
ይህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የወጣቶችን የእርስ በርስ ትስስርና አንድነት ከማጠናከሩ ባለፈ፣ በመንግሥት በጀት ያልተሸፈኑ የልማት ሥራዎችን በማከናወን የብዙዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ማቃለል እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።