ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ የማቋቋም ርዕይ ሀገሪቱን የአፍሪካ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ማዕከል ያደርጋታል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ (AIU) የማቋቋም ርዕይ ሀገሪቱን የአፍሪካ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ማዕከል የሚያደርግ ታሪካዊ እርምጃ መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት የትምህርት ክፍል ኃላፊ ሶፊያ አሺፓላ ገለጹ።

ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ ለማረጋገጥ ዲጂታል ቴክኖሎጂን የኢኮኖሚ ምሰሶና የልማት ማሳለጫ መሣሪያ በማድረግ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች። 

የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂና የአምስት ሚሊዮን ኢትዮ-ኮደርስ መርሐ ግብርም የዜጎችን የዲጂታል፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎትና የዳታ ሳይንስ ዕውቀትና ክህሎት የሚያበለጽግ አቅም እየፈጠሩ ነው።

የዲጂታላይዜሽን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም የመንግሥት አገልግሎቶችን ጥራትና ተደራሽነት በማረጋገጥ በቁልፍ የኢኮኖሚ መሣሪያነት በማገልገል ስኬት አስገኝቷል። 

የአፍሪካ ኅብረት የትምህርት ክፍል ኃላፊ ሶፊያ አሽፓላ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ መስክ ወሳኝ መደላድል በመፍጠር አበረታች ውጤት እያመጣች ነው። 

በተለይም የሰው ሠራሽ አስተውሎትን ልማት ለማፋጠን ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም የወሰደችው ተነሳሽነት ከፍተኛ አድናቆት የሚቸረው መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የተጀመረው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ልማት አብዮትም በሌሎች የአፍሪካ አገራት ተመሳሳይ ኢንቨስትመንቶች እንዲስፋፉ በር የሚከፍት ታሪካዊ ክስተት እንደሆነ አንስተዋል።

ይህም በአፍሪካ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ልማት የለውጥ ጉዞ ላይ ትልቅ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ የማቋቋም ርዕይ የወደፊቱን ትምህርትና ምርምር በተሻለ ጥራት በመቅረጽ አገሪቱን ፈር ቀዳጅ እንደሚያደርጋት አስረድተዋል።

ይህም የሰለጠነና ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት፣ በአፍሪካ የፈጠራ፣ የምርምርና የሰው ኃይል ልማትን የሚያፋጥን ዓለም አቀፍ የልማት አብዮት መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የትምህርት መሠረተ ልማትን የማስፋፋት ተግባር የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማረጋገጥ ለአፍሪካ አገራት ጭምር በአርአያነት የሚወሰድ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በአንደኛና በቅድመ-አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ውጤታማነትም ሕፃናትንና ታዳጊዎችን በተሻለ ዕውቀትና ክህሎት በማበልጸግ ሀገር ተረካቢ ዜጋን ለማፍራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም