ቀጥታ፡

ስብራትን የጠገነ፤ ተስፋንም ያለመለመ በጎነት

የበጎነት ኃይል፤ የአቶ ጥላሁን አበበና ቤተሰቡ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ በታደሰችው አዲስ አበባ ሰማይ ሥር በበጎነት ሲገለጥ!!

"እንኳን ደስ አለዎት፤ ቤትዎ ደርሷል፤ በሰላም ይግቡ!!"

አቶ ጥላሁን አበበ ይህን ዜና በሰሙበት ቅጽበት ለጥቂት ደቂቃዎች መናገር አልቻሉም። በዐይናቸው ተቋጥሮ በጉንጫቸው የሚወርደው እንባ የደስታ ብቻ አልነበረም። የዓመታት መከራ፣ የተበተነ ቤተሰብ፣ በሸራ ሥር የተደረገ የሕይወት ትንቅንቅና በተስፋ ብቻ የተገፋ ሕይወት ሁሉ በአንድ ቅጽበት በፊታቸው ተደቀነ።

ዛሬ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የልጆቻቸው ሳቅ ይሰማል። የቤቱ ግድግዳ የድህነትን ጩኸት በደስታ ቀይሮታል። ይህ የተገነባው ቤት ብቻ ሳይሆን፣ የተሰበረ ልብና ተስፋም ጭምር ነው።

የሕይወት ፈተና፡- አቶ ጥላሁን በ1963 ዓ.ም. በአማራ ክልል ደሴ ዙሪያ አማራ ሳይንት ተወለዱ። ልጅነታቸውን እንደ ብዙ የገጠር ልጆች ሁሉ በጨዋታ፣ በከብት እረኝነትና በፈረስ ግልቢያ አሳለፉ። ነገር ግን በ12 ዓመታቸው ከፈረስ ላይ በወደቁበት አደጋ የሕይወታቸውን መንገድ ቀየሩት። በዚህም ቀኝ እጃቸው ከባድ ጉዳት አስተናገደ። ከዚያ በኋላ የአካል ጉዳተኝነት የዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ሆነ።

ይህ ብቻ አልበቃ አለ። በዚያ የለጋነት ዕድሜያቸው እናታቸውን በሞት አጡ። ቤተሰባቸውም ሌላ ፈተና ውስጥ ወደቀ። በዚያ ዕድሜ ብዙዎች ተስፋ ይቆርጣሉ፤ እርሳቸው ግን የያዙት ተስፋ ነበር።

"እጄን ለልመና ከመዘርጋት ይልቅ በሥራዬ መኖር ይገባኛል" የሚለው ጽኑ ሃሳባቸው በ1979 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ አመጣቸው። ከተማዋ ማንንም በቀላሉ አትቀበልም። በተለይ አንድ እጁን ያጣ ወጣት ለመኖር እጅግ ፈታኝ ነበር። ሆኖም የቻሉትን ሁሉ ሠሩ፤ በአንድ እጃቸው ሕይወትን ለማሸነፍ ቀንና ሌሊት ታገሉ።

የሰቀቀኑ ዘመን፡- ትዳር መሠረቱ፤ የአምስት ልጆች አባት ሆኑ። ነገር ግን የመኖሪያ ቤት እጦት የቤተሰቡን ደስታ በእጅጉ መፈታተኑን ቀጠለ። ይህ የብዙዎች የዘመናት እጣ ፈንታ ነበር። አቶ ጥላሁንም የዚሁ ሰለባ ሆኑ። አንዳንዴ ልጆቹ ዘመድ ቤት ያድሩ ነበር። አንዳንዴም ወደ ገጠር ይላካሉ። እርሳቸውም በሚሠሩበት ቦታ ሁሉ ሸራ ዘርግተው ያድራሉ። ለአንድ አባት ከልጆቹ ጋር አብሮ አለመኖር ከማንኛውም ድህነት በላይ የሚከብድ ነው።

የቤት ተስፋ ግን አልጠፋም። ስማቸውን በብዙ የአዲስ አበባ የወረዳና የቀበሌ መስተዳድሮች አስመዘገቡ። ዓመታትን ጠበቁ፤ በትዕግሥትም ኖሩ።


 

ተስፋ የለመለመበት ምዕራፍ፡- ተስፋ ያለመለመው በጎነት እንዲሉ፣ 2015 ዓ.ም. ለአቶ ጥላሁንና ለቤተሰባቸው አዲስ የሕይወት ምዕራፍን የከፈተችበትን አጋጣሚ ፈጠረች። በአዲስ አበባ ከተማ በበጎ ፈቃድና በማኅበራዊ ድጋፍ መርሃ ግብሮች አማካኝነት የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ሆኑ።

"ምስጋና ለፈጣሪ ይሁን። ይህ በጎ ተግባር ከነበርኩበት ማኅበራዊ ቀውስ አውጥቶ ብሩህ ሕይወት እንድመራ አስችሎኛል" ሲሉ የሚናገሩት ቃላቸው ከልባቸው ነው። ምክንያቱም የተበተነው ቤተሰባቸው ዳግም በአንድ ጣሪያ ሥር ተሰብስቧል፤ የተሰበረ ልባቸውና ተስፋቸውም ተጠግኗል።


 

ባለቤታቸው ወይዘሮ ዓይናለም ታረቀኝ እንደሚሉት፤ የቤቱ መገኘት ቤተሰቡን እንደገና ወልዶታል። "ከዚህ በፊት ልጆቻችን ተበታትነው ነበር፤ አሁን ግን አብረን እንኖራለን። የነበረው ጭንቀት ቀርቷል፤ ሕይወታችንም ተቀይሯል" ይላሉ። 

ልጃቸው አክሊሉ ጥላሁንም የልጅነት ትዝታውን ሲያስታውስ፣ "አባቴን በሥራ ቦታው እየተከተልኩ ብዙ መከራ አይቻለሁ። ዛሬ ግን አንድ ቤት ውስጥ መኖራችን ትልቅ ደስታ ነው" ይላል።

በጎነት የሕይወት ትርጉም ነው፡- የአቶ ጥላሁን ታሪክ የአንድ ሰው ታሪክ ብቻ አይደለም፤ እንደ ዋርካ በገነኑ ሕንፃዎች ግርጌ የዘመሙ ጎጆዎች ታሪክም ጭምር እንጂ። የበጎነት ኃይል የሰውን ሕይወት በብርሃን ፍጥነት ይቀይራል። የአቶ ጥላሁን ቤተሰብ የሕይወት ዑደትም ሕያው ምስክር ነው።

በጎነት ግድግዳ ብቻ አትገነባም፤ የተሰበረን ተስፋና ልብን ታድሳለች። የተበተነን ቤተሰብ ታሰባስባለች። የአቶ ጥላሁን ቤት የተገነባው በሲሚንቶና በጡብ ብቻ አይደለም፤ በመረዳዳት፣ በአብሮነትና ሰውን ሰው አድርጎ በማየት ነው።


 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማኅበረሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ምክትል ኮሚሽነር አስራት ንጉሴ እንደሚገልጹት፣ በበጎ ፈቃድ የሚከናወኑ ተግባራት የበርካታ ዜጎችን ችግር ከመቅረፍ ባሻገር፣ የኢትዮጵያውያንን የመረዳዳትና የአብሮነት እሴት እያጠናከሩ ይገኛሉ።

እንደ አቶ ጥላሁን ያሉ ታሪኮችም የዚህ እውነታ ሕያው ምስክሮች ናቸው። በጎነት እጅ ሲዘረጋ የሚቀየረው የአንድ ሰው ኑሮ ብቻ አይደለም። የአንድ ቤተሰብ እጣ ፈንታ፣ የአንድ ማኅበረሰብ ተስፋና የአንድ ሀገር የአብሮነት መንፈስም ጭምር ነው። የዚህ ታሪክ ትልቁ ትምህርትም ይኸው ነው። አንድ የበጎነት እጅ ለአንድ ሰው ቤት ብቻ አይሰጥም፤ የነገን ሕይወትም ይገነባል።

በጎነታችን ለአብሮነታችን፣ አብሮነታችን ለተሻለ ተስፋችን!

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም