የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባዔ የዳኞች ሹመት በማፅደቅ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባዔ የዳኞች ሹመት በማፅደቅ ተጠናቀቀ
አዳማ፣ሐምሌ 13/2018 (ኢዜአ)፦የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የሥራ ዘመን 5ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ጉባዔ የክልሉን ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርት ማዳመጥን እና የዳኞች ሹመትን በማፅደቅ ተጠናቋል።
በጉባዔው ላይ የክልሉን ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ኃላፊ አቶ ተፈሪ ወንድይፍራው እንደገለጹት፥ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በተከናወነው የኦዲት ሥራ ሊባክን የነበረ የመንግሥት እና የሕዝብ ሀብት ተመላሽ ማድረግ ተችሏል።
የኦዲት ተደራሽነትና ሽፋኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ያመለከቱት ኃላፊው፣ በፋይናንስ ኦዲት፣ በገቢ ግብር፣ በታክስና በሊዝ አሰባሰብ እንዲሁም በዓይነትና በአካባቢ ኦዲት ላይ ጥሩ አፈጻጸም የተመዘገበበት የበጀት ዓመት እንደነበር አስረድተዋል።
አቶ ተፈሪ አክለውም፥ ጨፌው ለሕዝብ ልማት የተመደበው በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል እያደረገ ያለውን ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ በበኩላቸው፤ በክልሉ የኦዲት ግኝቶች ውጤታማ በሆነ መልኩ ምላሽ እንዲያገኙ የክልሉ መንግሥት ተገቢውን ድጋፍና እገዛ ማድረጉን ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተመዘገበው ውጤት ሊገኝ የቻለው የመንግሥት ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በሙሉ አቅማቸው በትብብር በመሥራታቸውና ለኦዲት መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊው ድጋፍ በመደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይም የኦዲት ግኝቶች በሙሉ ተመላሽ እንዲሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብርና በሙሉ አቅማችን እንሠራለን ብለዋል።
በጉባዔው ማጠቃለያ ላይ ጨፌው የዳኝነት ሹመቶችን ያጸደቀ ሲሆን፣ ዛሬ ከተሾሙት 94 ዳኞች መካከል 30 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው ታውቋል።