በአማራ ክልል በ42 የተለያዩ ከተሞች የኮሪደር ልማት ስራ ተከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በ42 የተለያዩ ከተሞች የኮሪደር ልማት ስራ ተከናውኗል
ባህር ዳር፤ ሐምሌ 13/2018 (ኢዜአ) ፡-በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ42 የተለያዩ ከተሞች የኮሪደር ልማት ስራ መከናወኑን የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የአማራ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ አማካሪ ሽቤ ክንዴ፤ በተለይም በከተሞች ልማት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተከናወኑ አበይት ተግባራትን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም በክልሉ ከተሞች የኮሪደር ልማት ስራዎችን በማስፋፋት ዘመናዊ በማድረግ ለኑሮ፣ ለኢንቨስትመንትና ለጉብኝት ጭምር ምቹ ማድረግ ስለመቻሉ አንስተዋል።
በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ42 የተለያዩ ከተሞች የኮሪደር ልማት ስራ ስለመከናወኑ ጠቅሰው በዚህም የዜጎችን ተጠቃሚነት እውን ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ የእግረኛ፣ የተሽከርካሪ፣ የብስክሌት መንገድን ጨምሮ የአረንጓዴ ልማት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ የመዝናኛ ስፍራዎችና መሰል አገልግሎቶችን አካቶ የተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በተያዘው በጀት ዓመትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
በልማቱ ከ214 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ስራ እንዲሁም ከ100 ሄክታር በላይ የተለያዩ አካባቢዎችን በአረንጓዴ ልማት የማስዋብ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በዚህ የልማት ስራ ከ199 ሺህ 700 ለሚበልጡ ወገኖች የስራ እድል ስለመፈጠሩ አንስተው ልማቱ ቀጣይነት ይኖረዋል ብለዋል።
የአንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት የልማት እንቅስቃሴም በ205 ከተሞችና ክፍለ ከተሞች 281 ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ሲሆን አብዛኞቹ ተጠናቀው ለህዝብ አገልግሎት እንዲውሉ መደረጉንም አንስተዋል።
በቀጣይም ልማቱን ወደ ሌሎች ከተሞች ለማስፋት መታቀዱን ያነሱት አቶ ሽቤ፤ የዜጎች እገዛና ተሳትፎ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።