ቀጥታ፡

በክልሉ የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች ከ97 በመቶ ተማሪዎች የማለፊያ ውጤት አስመዝግበዋል

ወራቤ፤ ሐምሌ 13/2018 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ተፈታኞች መካከል ከ97 በመቶ በላይ የሚሆኑት ተማሪዎች የማለፊያ ውጤት ማስመዝገባቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው የ2018 የትምህርት ዘመን የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ውጤትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ እንዳሉት፤ በክልሉ የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች ውስጥ 97 ነጥብ 4 በመቶዎቹ የማለፊያ ውጤት አስመዝግበዋል።

በክልሉ የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ከወሰዱ 85 ሺህ 531 ተማሪዎች ውስጥ 83 ሺህ 342 ተማሪዎች የማለፊያ ነጥብ ማስመዝገብ መቻላቸውንም አስረድተዋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

አዲሱን የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ መሠረት ያደረገ ጠንካራ የመማር ማስተማር ሂደትን በመፍጠር፣ ተማሪዎች በራሳቸው የሚተማመኑና ኩረጃን የሚጸየፉ ብቁ ዜጎች እንዲሆኑ የማድረግና ጠንካራ የፈተና አስተዳደር ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉንም ነው የተናገሩት፡፡

በመምህራን አቅም ግንባታ፣ በማጠናከሪያ ትምህርት ድጋፍና ማኅበረሰቡን በማሳተፍ የትምህርት ቤት ከባቢን ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ በማድረግ እንዲሁ በክልል አቀፍ ፈተናው ከፍተኛ ውጤት እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል፡፡

በክልሉ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ያማከለ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ በትምህርት ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመዘገቡ የሚገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ የማስቀጠል ሥራው በልዩ ትኩረት እንደሚመራም አቶ አንተነህ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም