ቀጥታ፡

የጤና አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ አምራች ዜጋ የመፍጠር ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል

አርባምንጭ ፤ሐምሌ 13/2018 (ኢዜአ) ፡-በሀገሪቱ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ አምራች ዜጋ የመፍጠር ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሀገሪቱ ከ41 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ "ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የጤና ምርመራና ህክምና አገልግሎት ዘመቻ" በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ላንቴ ቀበሌ ዛሬ ተጀምሯል።


 

በማስጀመሪያ ስነ ስርአቱ ላይ የጤና ሚኒስትር ደኤታ ከፍተኛ አማካሪ  ሌሊሳ አማኑኤል እንደገለጹት ሚኒስቴሩ የዜጎችን ጤና አገልግሎት በማጠናከር በሀገሪቱ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴዎች እንዲሳኩ በትኩረት እየሰራ ነው ።

ባለፉት ዓመታት በመደበኛው የጤና አገልግሎት በተከናወኑ  ተግባራት የተገኙ ውጤቶችን ለማጠናከር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል ።

በዚህም  በስምንት ክልሎች በሚገኙ በ401 ወረዳዎች ተግባራዊ የሚደረግ የጤና ምርመራና ህክምና አገልግሎት ዘመቻ መጀመሩን ተናግረዋል።

በዘመቻው ከ41 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁመው ለአስር ቀን በሚቆየው ሀገር አቀፍ ዘመቻ የወባና ትኩሳት፣ የቲቢ፣ የትራኮማ፣ የዝሆኔ ጤና ምርመራና ህክምና እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል።

እንዲሁም  የማህፀን ጫፍ ካንሰር ቅድመ ምርመራና  የተቀናጀ የጤና ትምህርት አገልግሎቶች እንደሚሰጥ አመልክተዋል ።

ለዘመቻው ስኬት በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻዎችና ህብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ  ጠይቀዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትልና የጤና ፕሮግራም ዘርፍ ሃላፊ አቶ መና መኩሪያ በበኩላቸው ዘመቻው በቁጥጥር ስር መዋል የሚችሉ በሽታዎች የሚያደርሱትን ጉዳት በተቀናጀ መልኩ ለመቅረፍ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘመቻው በክልሉ በስምንት ዞኖች በሚገኙ 25 ወረዳዎች ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመው  ለውጤታማነቱ የጤና ኤክስቴንሽን፣ ከፍተኛ የጤና ባለሙያዎች፣ የተደራጁ የሴቶች ህብረት ቡድን እና አጋር አካላት በቅንጅት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።


 

የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የስራና ክህሎት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሐኪሜ አየለ በዞኑ በአርባምንጭ ዙሪያ፣ጋጮ ባባና ቦረዳ ወረዳዎች ዘመቻው ስኬታማ እንዲሆን በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በማስጀመሪያ ስነ ስርአቱ ላይ የጤና ሚኒስቴር ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፣ የጋሞ ዞን እና የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የስራ ሃላፊዎች ፣የሃይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ነዋሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ተሳታፊዎቹ አረንጓዴ አሻራቸውንም አኑረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም