ቀጥታ፡

በድሬደዋ ከ71 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወሰዱ

ድሬደዋ፣ሐምሌ 13/2018 (ኢዜአ)፦በድሬደዋ አስተዳደር በበጀት አመቱ ከ71 ቢሊዮን ብር በላይ ያስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን የአስተዳደሩ ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ።

በቢሮው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ጥናት፣ መረጃ ዝግጅትና ፕሮሞሽን ቡድን አስተባባሪ አቶ አበራ መንግስቱ ዛሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አስተዳደሩ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት በቀየሰው ምቹ ሁኔታ በበጀት አመቱ ከ71 ቢሊዮን 304 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 464 ባለሃብቶች ፈቃድ ወስደዋል።

በአምራች ኢንዱስትሪ፣በአገልግሎት፣በኮንስትራክሽንና በግብርና ዘርፎች ፈቃድ የወሰዱት አልሚዎችም ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገቡ ከ21 ሺህ 650 በላይ ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ይፈጥራሉ ብለዋል።

አስተዳደሩ አልሚዎቹን ውጤታማ ለማድረግ መሠረተ ልማቶችን ከማሟላት ባሻገር ክትትልና ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በአስተዳደሩ የተተገበረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፣የተቀናጀ ድጋፍ እና ክትትል የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት በማሳደግ ተኪ ምርቶችን ማሳደግና የውጭ ምንዛሬን ማስፋት መቻሉን ጠቅሰዋል።


 

በዚህም በርካታ ኢንዱስትሪዎችም ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማደግ እንደቻሉና ለዜጎችም የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ ማገዙን ገልጸዋል።

ይህም ድሬደዋን በኢንቨስትመንት ዘርፍ የምስራቅ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ማዕከልነቷን ከማሳደግ በላይ የአስተዳደሩን ማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ደረጃ ማሳደጋቸውን ተናግረዋል።

በኢንቨስትመንት ዘርፉ ፈቃድ ወስደው እንቅስቃሴ ለጀመሩ ባለሃብቶች ከአስተዳደሩ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ጋር በመቀናጀት ከ50 ሄክታር መሬት በላይ መቅረቡን አቶ አበራ ጠቁመዋል።

ኢንቨስትመንቱን ለማስፋትም የመስሪያ ማሽኖችን ከታክስ ነፃ እንዲያስገቡ መደረጉንና የፋይናንስ፣የውሃ፣ የመንገድና የኤሌክትሪክ አገልግሎቶች እንዲሟሉ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በትብብር መሰራቱን አንስተዋል።

በሆቴልና በቡና ማቀናበር ዘርፍ ፍቃድ ከወሰዱ ባለሃብቶች መካከል አቶ ተካልኝ አበበ እና አቶ አብዱልጀባር አሊ በበኩላቸው፥ አስተዳደሩ ለባለሃብቶች እየፈጠረ የሚገኘው ምቹ የስራ አካባቢና የሚያደርገው ድጋፍ አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም