ቀጥታ፡

በሀገራዊ ምክክሩ ለዜጎቿ ሁሉ የምትመች ሀገር ለመገንባት የሚያስችል ታሪካዊ አጋጣሚ ላይ እንገኛለን

ጅማ፤ ሀምሌ 13/2018(ኢዜአ)፡- በሀገራዊ ምክክሩ ለዜጎቿ ሁሉ የምትመች ሀገር ለመገንባት የሚያስችል ታሪካዊ አጋጣሚ ላይ እንገኛለን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከህዝብ የሰበሰባቸውን አጀንዳዎች ለይቶ እና አደራጅቶ ለምክክሩ ይፋ ባደረጋቸው አጀንዳዎች ላይ በአዲስ አበባ የምክክር ጉባኤ በማካሄድ ላይ መሆኑ ይታወቃል።

የምክክር ሂደቱ የኢትዮጵያን የቆዩ ስብራቶች በማከም የጸናችና ለትውልዱ የምትመች ሀገር ለመገንባት ጠንካራ መሰረት ለማኖር የሚያስችል እንደሚሆን ይታመናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በምክክር ጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር በምክክሩ ከየሰፈራችን ወጥተን ለኢትዮጵያ ስንመክር፣ ለልጆቻችን ስንልና እነርሱን እያሰብን ስንወያይ ውጤቱ ፍሬያማ ይሆናል ማለታቸው ይታወቃል።

በመሆኑም የምክክሩን ውጤት ስኬታማ በማድረግ የኢትዮጵያን ሀገረ መንግስት ማጽናትና ለዜጎቿ ሁሉ የምትመች ሀገር ለመገንባት የሚያስችል ታሪካዊ አጋጣሚ ላይ እንገኛለን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገልጸዋል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ጌታቸው ጥላሁን (ዶ/ር)፤ የመነጋገር ባህል ሲዳብር በውይይት የሚያምን ዘመናዊና ጠንካራ ትውልድ የሚፈጠር ይሆናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከምክክር ይልቅ በሃይልና በጉልበት ለግጭትና ጦርነት የተዳረግንበት አጋጣሚ የበዛ ነው ያሉት ዶ/ር ጌታቸው፤ ሀገራዊ ችግሮችን ለመቋጨት ከምክክር የተሻለ አማራጭ አይኖረንም ብለዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን ሀገረ መንግስት ማጽናትና ለዜጎቿ ሁሉ የምትመች ሀገር ለመገንባት የሚያስችል ታሪካዊ አጋጣሚ ላይ በመሆናችን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በምክክር ኮሚሽኑ የተለዩ አጀንዳዎችን ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉ ቁልፍ ነጥቦች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ውጭ ግንኙነት መምህር ነጋሳ ገላና፤ ከግጭትና የጦርነት አዙሪት በመውጣት ለዜጎቿ የምትመች ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት በምክክር ኢትዮጵያን ማጽናት ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ምክክሩ  ነፃ አካታችና ሁሉንም አሳታፊ በሆነ መልኩ እየተካሄደ በመሆኑ ትልቅ ስኬት የሚመዘገብበት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተለዩ የምክክር አጀንዳዎች የኢትዮጵያን ችግሮች በአግባቡ የለዩና በምክክር መፍትሄ ሊያመጡ የሚችሉ ስለመሆናቸው አንስተዋል።

ሀገራዊ ምክክር የውስጥ ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት መንገድ ስለሚከፍት፣ መበታተናችንን የሚሹ አካላት በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡበትን ቀዳዳ የሚዘጋ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም