የምክክር ሂደቱ ለኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ መፃኢ እድል ትልቅ ተስፋ የተሰነቀበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ሂደቱ ለኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ መፃኢ እድል ትልቅ ተስፋ የተሰነቀበት ነው
ጎንደር፤ ሃምሌ 13/2018(ኢዜአ)፡- የምክክር ሂደቱ ለኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ መፃኢ እድል ትልቅ ተስፋ የተሰነቀበት በመሆኑ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከህዝብ የሰበሰባቸውን አጀንዳዎች ለይቶ እና አደራጅቶ ለምክክሩ ይፋ ባደረጋቸው አጀንዳዎች ላይ በአዲስ አበባ የምክክር ጉባኤ በመካሄድ ላይ መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያን የቆዩ ስብራቶች በማከም የጸናችና ለትውልዱ የምትመች ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ምክክሩ አዲስ የታሪክ ምእራፍ የሚከፍት መሆኑ ይታመናል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ በጎንደር ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የኃይማኖት አባቶች የምክክር ሂደቱ ለኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ መፃኢ እድል ትልቅ ተስፋ የተሰነቀበት በመሆኑ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኃይማኖት አባት መላከ ገነት ቀሲስ ፈንታ ገብረሚካኤል፤ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ከምክክር የሚሻል አማራጭ የለም ሲሉ ተናግረዋል።
በምክክር ችግሮች ሲፈቱ ነጋዴው ነግዶ የሚያተርፍበት፣ ገብሬው አርሶ የሚያመርትበት፣ የትኛውም ዜጋ ተንቀሳቅሶ ሃብት በማፍራት ለሀገር እድገት የድርሻውን የሚወጣ ይሆናል ብለዋል።
በመሆኑም ከጥላቻና የከረረ ተቃርኖ በመውጣት በምክክር ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል ጠንካራ አቋም በመያዝ ለስኬታማነቱ መስራት ይገባናል ሲሉ ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ሐሰን ደሴ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ከግጭትና ጦርነት አዙሪት ልንወጣ ያልቻልነው ለምክክር ቦታ በመስጠት ችግሮችን መፍታት ባለመቻላችን ነው ብለዋል።
በመሆኑም ሀገራዊ የምክክር ሂደት መካሄዱ ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ ትልቅ እድል መሆኑን አንስተው በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ብዝሃ ማንነቶችና ሃይማኖቶች ያሉ በመሆኑ በልዩነቶች ውስጥ መመካከርና መደማመጥ የግድ መሆኑንም አንስተዋል።
የካዶሽ ወንጌላዊያን አማኞች ጎንደር አጥቢያ መጋቢ የሆኑት መጋቤ እልፍነህ ተስፉ፤ የሀገርን አንድነት ማስቀጠል የሚቻለው በምክክር ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ በመስጠት ብቻ ነው ብለዋል።
ሌሎች ብዝሐ ማንነት ያላቸው ሀገሮች ችግር በገጠማቸው ጊዜ ተግዳሮታቸውን የፈቱት በምክክር እንጂ በጦርነት አለመሆኑን አንስተው እኛም ይህንኑ የምክክር እድል በአግባቡ መጠቀም አለብን ሲሉ ተናግረዋል።