ምክክር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነት - ኢዜአ አማርኛ
ምክክር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነት
ረጅም ታሪክ፣ቱባ ባህልና ሕብረ-ብሔራዊነት መለያዋ የሆኑት ኢትዮጵያ፣ የነገ ተስፋዋን አስተማማኝ ለማድረግ አዲስ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል ይበልጥ ብሩህ ለማድረግ ሀገራዊ ምክክር ቁልፍና ታሪካዊ ሚና ይጫወታል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በመላ ሀገሪቱ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ አጀንዳዎችን የመሰብሰብ አጠናቆ ዋናውን ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በይፋ ማካሄድ ጀምሯል።
ኮሚሽኑ በመላ ሀገሪቱ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰበሰቡትን ሀሳቦችን በማደራጀት ለዋናው ሀገራዊ ምክክር በቀረቡት ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ምክክር እየተካሄደ ነው።
የተለዩትን መሠረታዊ አጀንዳዎች መነሻ በማድረግ የሚደረገው ውይይት፣የፖለቲካ መረጋጋትን ከመፍጠር ባለፈ ለአስተማማኝ የኢኮኖሚ እድገትና ለጠንካራ ተቋማት ግንባታ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
ምክክሩ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ያለው ፋይዳ እጅግ የጎላ ነው።ባለፉት የታሪክ ሂደቶች የተፈጠሩ ቅሬታዎችን በጠረጴዛ ዙሪያ በሰላማዊ ውይይት በመፍታት፣እርስ በርስ ለመደማመጥ እና ታሪካዊ ቁስሎችን በይቅርታ ለመፈወስ የሚያስችል ዋነኛ መንገድ ነው።
ከጠመንጃና ከኃይል አማራጭ ይልቅ የሀሳብ የበላይነት የሚነግስበትን፣አለመግባባቶችና ልዩነቶች በሰላማዊ ውይይትና በንግግር የሚፈቱበትን ባህል ያሰፍናል።ይህም ልዩነቶችን በመቀበል በአንድነትና በጋራ መኖር የሚያስችሉ የጋራ እሴቶችና ሀገራዊ መግባባቶች ለማጠናከር ይረዳል።
ከዚህም ባለፈ፣ምክክሩ ለተቋማዊ እድገትና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዋነኛ ምሰሶ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ ስምምነት ላይ ለመድረስ መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በተከፈተበት እለት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ኢትዮጵያ በገዛ እጇ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የሚያስችላትን “ብዕርና ብራና” ያገኘችበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ሲሉ ገልጸውታል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፣ አብረን ተስፋን፣ ይቅርታን እና በጋራ መኖርን እንትከል፤ በሀገር ውስጥ በሚደረግ ውይይትና ይቅርታ ችግሮቻችንን በመፍታት ሀገራችንን ከውጭ ጣልቃ ገብነት እንጠብቅ በማለት አሳስበዋል።
ተሳታፊዎች በሙሉ ለኢትዮጵያ መልካም፣ ለአፍሪካ አስተማሪ፣ ለመላው ኢትዮጵያውያን ደግሞ እውነተኛ እረፍትን የሚያመጣ ታሪካዊ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህንን በጎ ዕድል ለመጠቀምም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንነትና በኃላፊነት ስሜት በመሳተፍ ለሀገር ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ ሀገራዊ ምክክር የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል በራስ አቅምና ጥበብ ለመወሰን የሚያስችል ትልቅ እድል ነው።የኢትዮጵያ መጻኢ ተስፋና ሁለንተናዊ ብልጽግና ከሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ጋር የተሳሰረ ነው።
ባለፉት የታሪክ ሂደቶች ውስጥ የተፈጠሩ ቅሬታዎችን በንግግር መፍታት፣ከኃይል አማራጭ ይልቅ የሃሳብ የበላይነት የሚነግስበትን ምቹ መደላድል ይፈጥራል።
ዛሬ በምክክሩ ጠረጴዛ ዙሪያ የሚታየው የመነጋገር እና የመደማመጥ ባህል እንዲሁም ችግሮችን በውይይት ብቻ የመፍታት አማራጭ የተሻለች ኢትዮጵያን እውን የሚያደርግ ታሪካዊ መሰረት ይጥላል።