ሀገራዊ ምክክሩ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት መሰረት ይጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት መሰረት ይጥላል
አርባ ምንጭ/ወላይታ ሶዶ፤ሐምሌ13/2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩ አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት መሰረት እንደሚጥል የአርባ ምንጭ እና የወላይታ ሶዶ ከተሞች ነዋሪዎች ገለጹ።
በሀገሪቱ ዘመናትን ያስቆጠሩ አለመግባባቶች በውይይት ለመፍታት ቁልፍ መሳሪያ የሆነው ሀገራዊ ምክክር በርካታ ሂደቶችን አልፎ ወደመቋጫ ምዕራፍ ደርሷል።
ኢዜአ ይህን ታሪካዊ መድረክ በማስመልከት የአርባ ምንጭ እና የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎችን አነጋግሯል።
አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች እንደገለጹት፥ ይህንን ሀገራዊና ታሪካዊ ምክክር በሰለጠነ መንገድ በመጠቀም ለውጤት ማብቃት የቆዩና ላለመግባባት መንስኤ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ አቶ ድኮርሳ ከበደ እንዳሉት፥ ምክክሩ የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ለማስቀጠል ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።
ለምክክር ተለይተው የቀረቡ አጀንዳዎችም የኢትዮጵያን የዘመናት ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉና ህዝቡ በየደረጃው በተዘጋጁ መድረኮች ያነሳቸውን መሰረታዊ ጥያቄዎችን ያንጸባረቁ ናቸው ብለዋል።
ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ኢንጂነር ጽዮን አረጋ በበኩላቸው፤ ምክክሩ ለነገው ትውልድ የተሻለችና የተረጋጋች ሀገር ለማውረስ ትልቅ ዕድል መሆኑን አንስተዋል።
በሃሳብ ልዕልና ላይ በመመስረት ልዩነቶችን ማስታረቅ የሚችል ስልጡን ማህበረሰብ ለመገንባት ምክክሩ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ጠንካራ ሀገረ-መንግስት ለመገንባት የምናደርገው የጋራ ጉዞ ነው ያሉት ደግሞ አቶ አየለ አፋ ናቸው።
የምክክር አጀንዳዎቹ ለዘመናት የቆዩ ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታትና በህዝቦች መካከል አንድነትን ለማጠናከር ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የተጀመረው ምክክር ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በጋራ ተወያየቶ ለመፍታት እና አንድነቷ የተጠናከረና የበለጸገች ሀገር ለማጽናት መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።
ከወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዋች መካከል ወይዘሮ የአብስራ ደለለኝ ለሀገራዊ ምክክሩ የተመረጡት አንኳር አጀንዳዎች በሀገሪቱ የቆዩ ቅሬታዎችን ለመፍታት የሚያግዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ምክክሩ በሀገር ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ወሳኝና ታሪካዊ ዕድል መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ አሸናፊ ዳንሳ ናቸው።
ለቀጣዩ ትውልድ ሰላሟ የጸና፣አንድነቷ የተረጋገጠና የበለጸገች ሀገር ለማስረከብ ሀገራዊ ምክክሩን ውጤታማ ማድረግና በስኬት ማጠናቀቅ የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።