ቀጥታ፡

በክልሉ የዳኝነት አገልግሎትን ዲጂታላይዝ የማድረጉ ተግባር አበረታች ውጤት እያስገኘ ነው

አዳማ፤ ሐምሌ 13/2018(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታላይዝ የማድረጉ ተግባር አበረታች ውጤት እያስገኘ መሆኑን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ጋዛሊ አባሲማል ገለጹ።


 

በ6ኛው የጨፌ ኦሮሚያ 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቧል።

ሪፖርቱን ያቀረቡት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ ጋዛሊ አባሲማል፤ በክልሉ ፍትሐዊና ተደራሽ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የፍርድ ቤቶች የማስፈጸም አቅም ከመጨመሩ ባሻገር  መዝገቦች ሳይጓተቱ በተቀመጠላቸው ጊዜ ውስጥ ተመርምረው ውሳኔ እንዲያገኙ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በተለይም የዳኝነት አገልግሎትን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ማካሄድ ባለጉዳዮች ከሩቅ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ በመደረጉ የባለጉዳዮችን እንግልትና ወጪ ማስቀረት እንደተቻለ ገልጸዋል።


 

ዜጎች ካሉበት ሆነው የፍትሕ ሂደቱን እንዲከታተሉና ምስክር እንዲያሰሙ በተዘረጋው የቴክኖሎጂ ሥርዓት ከ181 ሺህ በላይ የክስ መዝገቦች ላይ ውሳኔ ማግኘታቸውንም ጠቅሰዋል።

ከዚህም ባለፈ የሐሰት ማስረጃዎች በተወሰነ መልኩ እየቀነሱ መምጣታቸውን ገልጸው፣ የሥነ-ምግባር ችግር ባለባቸው ዳኞች ላይም እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስረድተዋል።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 318 የሕግ ጥሰትና የዳኝነት ሥነ-ምግባር ጉድለት በፈጸሙ አካላት ላይ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቱ በበጀት ዓመቱ ከ500 ሺህ በላይ መዝገቦች ላይ ውሳኔ በመስጠት የዓመታዊ ዕቅዱን 97 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል፣ በክልሉ በሥራ ላይ የሚገኙ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች እየሰጡ ባሉት አገልግሎቶች በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ላይ የነበረው ጫና ከመቀነሱ ባለፈ አለመግባባቶች በሀገር በቀል እሴት መፍትሔ እንዲያገኙ ሆኗል ብለዋል።

በተመሳሳይ ሴቶች፣ ሕፃናትና አቅመ ደካሞች ነፃ የሕግ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም