ቀጥታ፡

በምክክር መግባባት ለኢትዮጵያ መፅናት

በኢትዮጵያ ለዘመናት ስር የሰደዱ የፖለቲካ ልዩነቶች ዛሬም ድረስ ሀገራዊ ችግሮች ሆነው በመቀጠላቸው በህዝቡ ማህበራዊ ትስስር፣በዘላቂ ሰላም፣በኢኮኖሚ ልማትና በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልጽግና ላይ ያሳደሩት አሉታዊ ተጽዕኖና ያስከተሉት ጠባሳ የጎላ ነው።

ይህም ልዩነቶች በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ካለመፈታታቸው የተነሳ ነው።

ለዚህ ነው በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ የቆዩ የፖለቲካ ችግሮችን እና አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት ተግባራዊ እንቅስቃሴ የተጀመረው።

ኢትዮጵያዊያንም ሀገራዊ ምክክርን ወደ የጋራ መግባቢያ መድረሻ መንገዳቸው በማድረግ እየተጠቀሙበት ይገኛል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም ከ4 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ሳያግባቡ የቆሙ ችግሮቻቸውን ተገናኝተው በመነጋገር እንዲፈቱ እድል አመቻችቷል።

ሀገራዊ ምክክሩ ከሐምሌ 8 ጀምሮ በአዲስ አበባ በስኬት እየተካሄደ ሲሆን ይዚህ ታሪካዊ ምክክርም ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት ያለምንም ልዩነት ሃሳባቸውን በነጻነት የሚያነሱበት እውነተኛ የአካታችነት ማሳያ ሆኗል።

በኢትዮጵያ የሐሳብ ገበያን ባሕል ለማድረግ ተግባራዊ ከሚደረጉ መንገዶች አንዱ ሀገራዊ ምክክር የሆነውም ለዚህ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት መጽሐፍ ገጽ 384 ላይ እንዲህ ይላሉ፦ በሀገረ-መንግሥት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ሕዝብ ተመካክሮ፣ የጋራ መግባባት ላይ ደርሶ፣ የተግባባባቸውን በሕግና በሥርዓት አጽንቶ፤ ያልተግባባባቸውን ለወደፊት ምክክሮች አቆይቶ አልተጓዘም።በዚህ የተነሣ በየጊዜው ቅሬታ፣ ኩርፊያ፣ አብዮት፣ ዐመጽ ይፈጠራል። ነገሮች በተናጠል እየቀረቡ ለፖለቲካ ነጋዴዎች ምቹ ሁኔታ ይመቻቻል። ሁለንተናዊ ዕይታ ይጠፋል።ሀገራዊ ምክክር ይህን የዘመናት ስብራት ይጠግናል።

በመደመር መንግሥት መጽሐፍ (ገጽ 383) ላይ እንደሰፈረው ደግሞ፤ በኢትዮጵያ የሚደረገው ሀገራዊ ምክክር የተለያዩ ሐሳቦች በአንድ መድረክ ቀርበው፤ በምክክርና ውይይት ጎልብተው አሰባሳቢና አስማሚ ሆነው የሚወጡበት መድረክ ነው። ስለሀገር የሚያገባው ሁሉም አካል በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ሐሳብ አዋጥቶና ተነጋግሮ መግባባት የሚፈጥርበት ምኅዳር መሆኑም ተገልጿል።

ይህ በሀገር በቀል ልምድና እውቀት ላይ የተመሰረተ ምክክር ለነገዋ ኢትዮጵያ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እጅግ የጎላ ስለሆነ ነው።በሂደቱ የሚደረጉ ውይይቶችና የሚደረሱ ስምምነቶች የሀገሪቱን ፖለቲካዊ መግባባቶች የሚያጠናክሩ ናቸው።

የጋራ ብሄራዊ ትርክት ለመገንባት፣ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ የህግ የበላይነትን ለማስፈንና የኢኮኖሚ ብልጽግናን ለማፋጠን መሰረት ይሆናሉ።

በመሆኑም ልዩነቶችን በውይይት ፈትቶ፣ለትውልድ ተስፋ የምትሆን፤በሰላምና በአንድነት የደመቀች ሀገር ለመገንባት ሀገራዊ ምክክሩ እጅግ አስፈላጊ ነው።

በዚህም ለጋራ ሀገር፤የጋራ ምክክር በማድረግ ልዩነቶች በውይይት በመፍታት ኢትዮጵያን ለማፅናት ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ እንዲሳካ ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም