የአዲስ አበባ ልማት ውጤቶች ለሰው ልጆች መኖሪያነት የሚገባን ክብር በተግባር የገለጡ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ልማት ውጤቶች ለሰው ልጆች መኖሪያነት የሚገባን ክብር በተግባር የገለጡ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ የተከናወኑ የልማት ውጤቶች ለሰው ልጆች መኖሪያነት የሚገባን ክብር በተግባር የገለጡ መሆናቸውን የክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚዎች ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ሶስት ተከታታይ ቀናት ሲያካሄድ የቆየውን የ2018 በጀት ዓመትና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በስኬት አጠናቋል።
በበጀት ዓመቱም ከተማ አስተዳደሩ በጥቅሉ ከ96 በመቶ በላይ የአፈጻጸም ውጤት ማስመዝገብ እንደቻለ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በግምገማ መድረኩ፤ በበጀት ዓመቱ ለመፈጸም የተቀመጡ ግቦች አመርቂ ውጤት እንደተገኘባቸው አስረድተዋል።
በግምገማው የተሳተፉት የአራዳና የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የመዲናዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት በማሳደግ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስኬቶች ተመዝግበዋል።
የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማቱም የመዲናዋን ዓለም አቀፍ ገጽታ በመገንባት፣ ለነዋሪዎቿ ተገቢውን ክብር የምትሰጥ ከተማ እንድትሆን ማድረጉን ገልጸዋል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወንድሙ ዑመር ፤ አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ክብር የሚሰጥ የከተማ ገጽታ በመላበስ፣ አስደማሚ የልማት ስኬቶች የሚመዘገቡባት ከተማ እየሆነች ነው ብለዋል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥና አዲስ የከተሜነት መኖሪያ ደረጃ ያሸጋገረ የልማት ባህል መፈጠሩን ገልጸዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኮሪደር፣ በወንዝ ዳርቻና በሰው-ተኮር የልማት መርሃ ግብሮች የተገኙ አመርቂ ውጤቶችም ነዋሪዎችን ከውስብስብ ችግሮች በማላቀቅ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ታረቀኝ ወርቅነህ በበኩላቸው፤ አዲስ አበባ ውብና ማራኪ ገጽታን የተጎናጸፈች የአለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን ገልጸዋል።
በመዲናዋ የተገነቡ ጽዱ፣ ውብና ምቹ የልማት ስኬቶች፣ በተለይም የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብርና ሌሎች ሰው-ተኮር ፕሮጀክቶች የዜጎችን ሕይወት በመቀየር ረገድ አመርቂ ውጤት ማስመዝገባቸውን አስረድተዋል።