ሁሉም ተቋማት የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን የበለጠ በማስፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ሁሉም ተቋማት የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን የበለጠ በማስፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁሉም ተቋማት የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን የበለጠ በማስፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ማስቀጠል እንደሚጠበቅባቸው ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተቋማት፣ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች "ትጋት ያሸልማል" በሚል መሪ ቃል የዕውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበጀት ዓመቱ የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎችን በመሥራት የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ቢሮዎች፣ ተቋማት፣ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ዕውቅናና ሽልማት አበርክተዋል።
በዚሁ መሰረት የካቢኔ አባል ከሆኑና ከተሽከርካሪ ተሸላሚ ከሆኑ ቢሮዎች መካከል ሰላምና ጸጥታ፣ ጤና፣ ገቢዎች፣ ዲዛይንና ግንባታ እንዲሁም የትምህርት ቢሮዎች ይገኙበታል።
የለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከልም ልዩ ሽልማት የተበረከተለት ሲሆን፤ በከተማ አስተዳደሩ የቦሌ፣ ለሚኩራና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች በተመሳሳይ የተሽከርካሪ ተሸላሚ ሆነዋል።
የካቢኔ አባል ያልሆኑት የደንብ ማስከበር ባለስልጣን፣ የመንገዶች ባለስልጣን፣ የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን፣ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ባለስልጣን፣ እንዲሁም የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ተሸከርካሪ ተሸልመዋል።
በተጨማሪም በሁሉም ክፍለ ከተማ ውስጥ ካሉ ወረዳዎች ከአንድ እስከ ሶስት የወጡ 33 ወረዳዎች ተሸላሚ ሲሆኑ፤ የፋይናንስ፣ የኢንዱስትሪ ልማት፣ የኮሙኒኬሽን፣ የንግድና ፍትሕ ቢሮዎችም የሰርተፍኬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት ፤ በ2018 በጀት ዓመት በተያዙ ዕቅዶች መሰረት ከ96 በመቶ በላይ የአፈጻጸም ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አስታውቀዋል።
የከተማ አስተዳደሩ መዋቅሮች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና በሌሎች መስኮች ላስመዘገቡት ውጤታማ የልማት አፈጻጸሞች ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም ሁሉም ተቋማት የተገኙ ስኬቶችን የበለጠ በማሳደግና ክፍተቶችን በመሙላት ለተሻለ የልማት ስኬት ገንቢ ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው፤ ህዝቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ ታላላቅ ኮንፈረንሶች፣ ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት በስኬት እንዲከበሩ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋማቸው የተሸለመው በኤሌክትሪክ የሚሰራ ተሽከርካሪ ለቀጣይ ሥራ ትልቅ ኃላፊነት የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ በበኩላቸው፤ የተበረከተላቸው የኤሌክትሪክ መኪና ሽልማት በጤናው ዘርፍ ለተመዘገበው ስኬታማ አፈጻጸም የተሰጠ ዕውቅና መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማው 68 የጤና ተቋማት የመረጃ አያያዝን ወረቀት-አልባ በማድረጋቸው እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት በተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አደፍርስ ኮራ በበኩላቸው፤ በክፍለ ከተማዋ የመዲናዋን ውብ ገጽታ የሚያላብሱ ስኬታማ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ክፍለ ከተማው የተሰጠው ሽልማትም የልማት አጋሮችን በማስተባበር በኮሪደር፣ በመንገድ፣ በወጣቶች መዝናኛና ስፖርት ማዘውተሪያ ላይ ላስመዘገበው የልማት ፕሮጀክቶች ስኬት የተሰጠ ዕውቅና መሆኑን ተናግረዋል።