ጨፌ ኦሮሚያ ለክልሉ መንግሥት የ2019 በጀት ዓመት ሥራ ማስፈጸሚያ 704 ቢሊዮን ብር በጀት አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
ጨፌ ኦሮሚያ ለክልሉ መንግሥት የ2019 በጀት ዓመት ሥራ ማስፈጸሚያ 704 ቢሊዮን ብር በጀት አጸደቀ
አዳማ፣ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦ጨፌ ኦሮሚያ ለተያዘው በጀት ዓመት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ዕቅድ ማስፈጸሚያ የሚውል 704 ቢሊዮን ብር በጀት በሙሉ ድምፅ አጸደቀ።
ጨፌ ኦሮሚያ በ6ኛ የሥራ ዘመን 5ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ጉባኤው የዛሬ ውሎ የክልሉን መንግሥት የ2019 በጀት አጽድቋል።
የኦሮሚያ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶሎሳ ገደፋ የበጀት ዝርዝሩን ለጨፌው ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ በጀቱ ከተረጂነት ለመውጣትና ራስን ለመቻል የተያዘውን ግብና ስትራቴጂ ለማሳካት ያለመ ነው።
የበጀት ድልድሉም የልማት ፕሮግራሞችን መሠረት በማድረግና የክልሉን ዕድገት ለማፋጠን በሚያስችል መልኩ ተከናውኗል ብለዋል።
የልማት ዕቅዱን ውጤታማ ለማድረግ ከሁሉም የክልሉ ሴክተር ተቋማት ጋር ውይይት መደረጉን የጠቀሱት ኃላፊው፤ ትኩረት ለሚሹ ጉዳዮች በበጀት ድልድሉ ቅድሚያ መሰጠቱን ተናግረዋል።
በጀቱ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ76 በመቶ ጭማሪ ያለው ሲሆን፣ የበጀት ድልድሉ የልማት ፕሮጀክቶችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በተለይም በከተሞችና በወረዳዎች ለሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል ብለዋል።
በዚህም መሠረት ለጤና፣ ለትምህርት እና ለመንገድ መሠረተ ልማት አንዲሁም ለመስኖ እና ለንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ቅድሚያ ተሰጥቷል ነው ያሉት።
ይህ በጀት በከተሞችና በወረዳዎች መካከል ሊኖር የሚችለውን የመሠረተ ልማት ልዩነት ለማጥበብና በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ ሰፋፊ መሬቶችን ለማልማት የሚያስችሉ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ታሳቢ ማድረጉንም ኃላፊው ገልጸዋል።
ከተሞችና ወረዳዎች የሚሰጣቸውን በጀት ለማኅበራዊ መሠረተ ልማት ማዋል ላይ ትኩረት አድርገው መደልደል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ማንኛውንም የገቢ ዓይነት ያለ ሕጋዊ ደረሰኝ መሰብሰብ የተከለከለና የሕግ ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆኑንም አሳስበዋል።
የጨፌው አባላት በቀረበው የበጀት ቀመር ላይ በሰጡት አስተያየት፤ የበጀት ድልድሉ ከተረጂነት ለመውጣትና ራስን ለመቻል የተያዘውን ግብ ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
ሆኖም ከበጀት ድልድሉ ባለፈ፣ የካፒታል በጀትን ጨምሮ የተመደበው ሀብት ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል ጠንካራ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።