ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡን የመደጋገፍ ባህል እያጎለበተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡን የመደጋገፍ ባህል እያጎለበተ ነው
ጅግጅጋ፤ ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡን የእርስ በርስ መደጋገፍና ግንኙነት እያጎለበተ መምጣቱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ገለጸ።
"በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ቃል የዘንድሮ ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊዎች በሶማሌ ክልል የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን አከናውነዋል።
ወጣቶቹ በጅግጅጋ ከተማ ደም ከመለገስ ባለፈ የአቅመ ደካማ ወገኖችን መኖሪያ ቤቶች የመገንባት መርሐግብር አከናውነዋል።
በመርሀግብሩ ላይ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር የበጎፈቃድ ከፍተኛ ባለሙያ እና የቡድኑ አስተባባሪ እንደገና ፍቃዱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚጠናከርበትና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች የሚከናወኑበት ነው።
ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ሀገር መሆኗን አስታውሰው፣ ወጣቶቹ ለአንድ ዓላማ መሰባሰባቸው ግንኙነታቸውን ከማጠናከር ባለፈ በሚደርሱባቸው አካባቢዎች የባህል ልውውጥ ለማድረግ ያስችላቸዋል ብለዋል።
የሚሰጡት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም የህብረተሰቡን ማህበራዊ ችግር በማቃለል አብሮነትን ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ነው የገለጹት።
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሀገሪቱ ሁሉም ክልሎች የተውጣጡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች በማከናወን ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በዚህም በተለይ በአካባቢ ጥበቃ፣ አቅመ ደካማ ወገኖችን በተለያየ መንገድ በመደገፍ እንዲሁም በትምህርት፣ በጤና እና በተለያዩ የልማት ዘርፎች በመሰማራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።