ቀጥታ፡

የትግራይ ሕዝብ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በትክክል ያንጸባረቀ ስኬታማ ሰልፍ ተካሂዷል 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦ የትግራይ ሕዝብ ድምጹን ያሰማበትና ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በትክክል ያንጸባረቀ ውጤታማ ሰልፍ መካሄዱን የትግራይ የሰላምና ለውጥ ምክር ቤት ገለጸ።

በትግራይ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን አፈና እና ጭቆና የሚያወግዝ እንዲሁም የጦርነት ዝግጅትን የሚቃወም ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ ተካሄዷል።

በትግራይ የሰላምና ለውጥ ምክር ቤት "አፈሳ ይቁም፣ ሰላም ይስፈን” በሚል መሪ ሐሳብ በተዘጋጀው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በአዲስ አበባና በአካባቢው የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች፣ የሲቪክ ማህበራትና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

ሰልፉን በተመለከተ የትግራይ የሰላምና ለውጥ ምክር ቤት መግለጫ ሰጥቷል።

የምክር ቤቱ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነጋ አሰፋ ሰልፉን በተመለከተ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ የትግራይ ተወላጆችና ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች በነቂስ በመውጣት ድምፃቸውን አሰምተዋል።

ሰላማዊ ሰልፉ የተለያዩ ዓላማዎችን አንግቦ የተካሄደ ሲሆን፤ ስኬታማ ሆኖ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ እየፈጸመ ያለው ድርጊት የትግራይን ሕዝብ በእጅጉ እንዳሳሰበው ገልጸው፤ ሰልፉ ስምምነቱ በአስቸኳይ እንዲተገበር የተጠየቀበት መሆኑን ተናግረዋል።

ወጣቶች ወደ ጦርነት እንዲገቡ እየተደረገ ያለው አስገዳጅ አፈሳ ወንጀል መሆኑን የገለጹት የምክር ቤቱ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነጋ፤ ይህንም ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የማሳወቅና ድርጊቱ በአስቸኳይ እንዲቆም መልዕክት የተላለፈበት ሰልፍ እንደነበር አብራርተዋል።

ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን እያደረገ ያለውን የጦርነት ዝግጅት እንዲያቆም የትግራይ ሕዝብ ግልጽ መልዕክት ያስተላለፈበት ሰልፍ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የሕዝቡን ተቃውሞ ለመመከት መድረኮችን እየጠራ በኃይል ለማስፈራራትና ለማስገደድ መሞከሩን ጠቁመው፤ ሕዝቡ ግን ለሰልፉ ያለውን ድጋፍ ቤቱ በመቀመጥ በተግባር አሳይቷል ብለዋል።

ሕዝቡ ትግራይን ድጋሚ ወደ ጦርነት ለመክተት እየተደረገ ያለውን ጥረት አጥብቆ እየተቃወመ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

የትግራይን ሰቆቃ ለማስቀረት የምንሰራውን ሥራ እናጠናክራለን ያሉት ኃላፊው፤ለዚህም ሁሉም በጋራ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

ሰልፉ እንዲሳካ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበው፣ መሰል የሕዝብ ድምፅ ማሰሚያ ሰልፎች በሌሎችም አካባቢዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም