ቀጥታ፡

ክልሎችን በወፍ በረር

ሀምሌ ፤ ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦ ክልሎችን በወፍ በረር

በዚህ ዝግጅታችን በሳምንቱ በክልሎች የተከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮችን በወፍ በረር በመቃኘት ማስታወስ ይሆናል። በመሆኑም በዚህ ሳምንት በሀገራችን ሁሉም ክልሎች ምን ምን ዋና ዋና ጉዳዮች ነበሩ ስንል እንጠይቃለን?

👉አማራ ክልል

የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ መመረቅ። ለ30 ዓመታት ያህል ተቋርጦ የነበረው የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያ በዘመናዊ መልክ ተገንብቶ በይፋ ተመርቋል። አወሮፕላን ማረፊያው 2 ሺህ 400 ሜትር ርዝመትና 30 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ እንደ Q400 እና B737 ያሉ ግዙፍ የሕዝብና የጭነት አውሮፕላኖችን ማሳረፍ ይችላል። ይህም የአካባቢውን ንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ያነቃቃል ተብሏል። በምርቃ መርሃ ግብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፌዴራል እና የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል።

👉ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል

"ትምህርት ለልጄ" የክረምት ንቅናቄ መካሄድ። በትምህርት ቤቶች ደረጃንና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ያለመ የ2018 ዓ.ም የክረምት ትምህርት ንቅናቄ መድረክ በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ ተካሂዷል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ተማሪዎች ብቁ ሆነው እንዲወጡ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻልና ግብዓት በማሟላት ረገድ በትኩረት መሠራቱን ገልጸዋል።

👉ድሬዳዋ

ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎችን በትክክለኛ መረጃ ላይ መስርቶ ለመቅረጽ የሚያስችል የዲጂታል ሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ሥርዓት በድሬዳዋ ተጀምሯል። ተግባሩ የተከናወነው በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እና በኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ሲሆን የተቋማቱ ዋና ዳይሬክተሮች ሰላማዊት ዳዊት እና ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) የተገኙ ሲሆን ይህ ሥርዓት የ"ዲጂታል 2030" ትግበራ አካል ነው።

👉ሶማሌ ክልል

ሰብዓዊ መብትና ሰላም ግንባታ ጉዞ። ‘ሰብዓዊ መብትና የሰላም ግንባታ’ በሚል መሪ ሐሳብ አገር አቀፍ የጸጥታና ፍትሕ አካላት ጉባኤ በጅግጅጋ ከተማ ተካሂዷል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በማረሚያ ቤቶች የሚገኙ የተጠርጣሪዎችና የታራሚዎች አያያዝ መሻሻል ማሳየቱን የጠቀሱ ሲሆን፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ በበኩላቸው በክልሉ ለሰላም፣ ለጸጥታና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

👉ሲዳማ ክልል

የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ስኬት- የ2018 ዓ.ም የሲቢኢ (CBE) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እና ከ20 ዓመት በታች ውድድር አሸናፊ ለሆነው የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የስፖርት ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ በየነ በራሳ የክለቡ ውጤት የአንድነትና የትጋት ማሳያ መሆኑን ገልጸው፣ ይህንን ስኬት በአርአያነት በመውሰድ በሌሎች የልማት መስኮችም መድገም እንደሚገባ አሳስበዋል።

👉ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል

የበጀት ዓመት ግምገማ። የ2018 በጀት ዓመት ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን እምቅ አቅሞችን በማልማት በሁሉም ዘርፎች የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መቻሉንና በቀጣይም አገራዊ ኢኒሼቲቮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። በተመሳሳይ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ በተፈጠረው "ንጋት ሐይቅ" ከተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ 10 ሺህ 799 ቶን ዓሳ ማምረት መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ብርሃኑ ኢትቻ(ዶ/ር) አስታውቀዋል።

👉አፋር ክልል

የገቢ አሰባሰብ ውጤት። በበጀት ዓመቱ ከ8 ቢሊዮን 524 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ አወል አብዱ ገልጸዋል። ለውጤቱ መገኘት በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር መዘርጋቱ፣ የግብር ከፋዩ ግንዛቤ ማደግና የአመራሩ ቁርጠኝነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

👉ሐረሪ ክልል

የበጀት አፈጻጸምና የ2019 በጀት መጽደቅ። የ2018 በጀት ዓመት የአስፈጻሚ አካላት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። ምክር ቤቱ የልማት ዕቅዶችን ለማሳካት ለ2019 በጀት ዓመት 12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በጀት አጽድቋል። ከበጀቱ ውስጥ ከፍተኛው ድርሻ ለካፒታል በጀት የተመደበ ሲሆን፣ ትኩረቱም ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅና የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ነው።

👉ኦሮሚያ ክልል

የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ሂደት። በ2018 በጀት ዓመት የመንግሥትና የፓርቲ ሥራዎች ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ የልማት ዕድሎችን፣ የሰው ኃይልንና ዕውቀትን አቀናጅቶ በመምራት ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል። በቀጣይም የተመዘገቡ ድሎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ከመደመር እሳቤ የተቀዱ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በላቀ ቁርጠኝነትና በሕዝብ ተሳትፎ መመራት እንዳለባቸው የሥራ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

👉ደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል 

የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት ከ150 ሚሊዮን 250 ሺህ ብር በላይ ከምዝበራ ማዳንና በኦዲት ግኝት ማስመለስ መቻሉን የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ሙሉሰው ዘውዴ አስታውቀዋል። ከዚህ ውስጥ 68.6 ሚሊዮን ብሩ በአስቸኳይ ሙስና መከላከል ሥራ ከምዝበራ የዳነ ነው።

ከገንዘብ በተጨማሪ 14 ሺህ 673 ካሬ ሜትር የከተማ መሬት እና 645 ሄክታር የገጠር መሬት፣ እንዲሁም በርካታ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብቶችን ማዳንና ማስመለስ ተችሏል። የአገልግሎት አፈጻጸሙን በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል ቅንጅታዊ አሠራርን ማሳደግ እንደሚገባም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም