በመዲናዋ የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና አቅርቦትን የሚያቀራርብ አማራጭ የቤት ልማት መርሃ ግብር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና አቅርቦትን የሚያቀራርብ አማራጭ የቤት ልማት መርሃ ግብር እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና አቅርቦቱን የሚያቀራርብ ስኬታማ የብዝኅ ቤት ልማት አማራጭ መርሃ ግብር እየተከናወነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ሶስት ተከታታይ ቀናት ሲያካሄድ የቆየውን የ2018 በጀት ዓመት እና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በስኬት አጠናቋል።
በበጀት ዓመቱም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጥቅሉ ከ96 በመቶ በላይ የአፈጻጸም ውጤት ማስመዝገብ እንደቻለ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በግምገማ መድረኩ ፤ በበጀት ዓመቱ ለመፈጸም የተቀመጡ ግቦች አመርቂ ውጤት እንደተገኘባቸው አስረድተዋል።
በግምገማው የተሳተፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በቤት ልማት ዘርፍ ውጤታማ ሥራዎች ተሰርተዋል።
ለአብነትም በመንግሥት፣ በግልና መንግሥት አጋርነት እንዲሁም በግል ባለሃብቶች ብዝኅ የቤት ልማት አማራጭ መርሃ ግብር የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና አቅርቦት የሚያቀራርብ ስኬታማ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህ ጥረትም ከዚህ ቀደም የነበረውን የቤት አቅርቦት እጥረት በመቅረፍ በመደመር እይታ አመርቂ የቤት ልማት ውጤት ማምጣት እየተቻለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በ2018 በጀት ዓመት በመንግሥት በጀት ብቻ ግንባታቸው የተጠናቀቁና በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ 50 ሺህ 305 ቤቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዳሴው ግድብ ምርቃት ወቅት ባበሰሩት የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቤቶች ግንባታ መርሃ ግብር፤ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ማስገንዘባቸው ይታወሳል።