ቀጥታ፡

በአማራጭ ኢነርጂ ማህበረሰቡን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አሶሳ፤ ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአማራጭ ኢነርጂ ተደራሽነትን በማስፋፋት ማህበረሰቡን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት እንደሚጠናከሩ  አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም አተገባበር ላይ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የዘርፉ አመራሮች እና ባለሙያዎች ጋር በአሶሳ ከተማ መክሯል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ አስተማማኝ፣ ተመጣጣኝና ቀጣይነት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት የመሰረተ ልማት ግብ ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ሕይወት ያቃልላል። 

የኃይል አቅርቦትን አስተማማኝ እና ተደራሽ ለማድረግ የኢነርጂ ፖሊሲ ወጥቶ ሥራ ላይ መዋሉን ገልፀው፣ ፖሊሲው የግሉን ዘርፍ የሚያበረታታ እና የኃይል ተደራሽነትን የሚያሳድግ መሆኑን አስረድተዋል።

ብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች የሶላር ኢነርጂ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ እና በደን ጭፍጨፋ በአካባቢ ላይ የሚደርስን ተፅዕኖ የሚቀንስ ነው ብለዋል።

አማራጭ የታዳሽ ኃይል ተደራሽነትን በማስፋፋት ህብረተሰቡን የሀይል ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ የኃይል መሠረተ ልማት ዝርጋታ እና አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ታሪኩ ኩመራ በበኩለቸው፤ በፕሮግራሙ በክልሉ የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች በገጠሩ አካባቢ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ መምጣታቸውን እና ይህም በርካታ ዜጎችን ከድካም መታደጉን ተናግረዋል።

የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን የሚያመርቱ ማህበራትን መደገፍ ዜጎች ማገዶ ፍለጋ የሚያባክኑትን ጊዜና ጉልበት ለመቀነስና የአየር ብክለትን ለመከላከል ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ጠቅሰዋል።

ለሁለት ቀን በሚቆየው መድረክ በክልሉ በአነርጂ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ላይ ምክክር እንደሚደረግ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም