በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ በዋና ዋና የልማት ዘርፎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ በዋና ዋና የልማት ዘርፎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበዋል
አዳማ፤ ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ በዋና ዋና የልማት ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸው ተገለጸ።
እየተካሄደ ባለው የጨፌ ኦሮሚያ 11ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የጨፌው አባላት የሰላም ማስፈንና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎችን የተመለከቱ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ መንግስት የተለያዩ ዘርፎች የሥራ መሪዎች በበጀት ዓመቱ ተስፋ ሰጪ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ፤ የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ በተከናወነው የተቀናጀ ሥራ የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ መጥቷል ብለዋል።
ህብረተሰቡ እና መንግስት በጋራ በሰሩት ሥራ የክልሉ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ለዚህም በክልሉ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
መንግስት የክልሉን የጸጥታ አካላት አቅም ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ሲሆን፣ ይህንን ለማሳካትም አቅም የመገንባትና የማብቃት ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
አሁንም በክልሉ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ የሚቀበሉ ከሆነ የክልሉ መንግስት ለመነጋገር ዝግጁ ሆኖ እየጠበቀ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ተወዳዳሪ ትውልድ ለማፍራት የጀመረው ሥራ ስኬታማ እየሆነ መምጣቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ ባሪሶ ገልጸዋል።
በክልሉ የትምህርት ሥራ በጥሩ ሂደት ላይ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፣ ተማሪዎች በሥነ-ምግባር ታንጸውና ብቁ ዜጋ ሆነው እንዲወጡ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል ብለዋል።
በተመሳሳይ በክልሉ የአርብቶ አደሩን ሕይወት ለመለወጥ በተከናወነው ሥራ አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን የክልሉ መስኖና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ግርማ ረጋሳ ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች 512 የመስኖ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን ገልጸዋል።
የክልሉ መንገዶችና ሎጂስቲክስ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ሄለን ታምሩ በበኩላቸው የሕዝቡ የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እየተመለሱ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም የኮንትራክተሮች አቅም ማነስ፣ የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ዋጋ ንረትና በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚታየው የጸጥታ ችግር ለመንገድ ፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያት እንደሆኑ ጠቅሰው፣ እነዚህን ችግሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመፍታት የመንገድ ስራዎችን ለማፈጠን ይሰራል ብለዋል።
የክልሉን የመጠጥ ውሃ ተደራሽነት ለማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ በተሰራው ስራ የክልሉን የንጹህ መጠጥ ውኃ ሽፋን ማሳደግ መቻሉን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ሚሊዮን በቀለ ናቸው።
ቢሮው ከመንግስት በጀት በተጨማሪ የማኅበረሰቡን እና የአጋር አካላትን ተሳትፎ በመጠቀም የመጠጥ ውሃ ሽፋንን ለማሳደግ ተጨባጭ ሥራ ሰርቷል ብለዋል።