የግብር አሰባሰብ አቅምን በማሳደግ የከተሞችን የመሰረተ ልማት ተደራሽነት በራስ አቅም ለማሳካት ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የግብር አሰባሰብ አቅምን በማሳደግ የከተሞችን የመሰረተ ልማት ተደራሽነት በራስ አቅም ለማሳካት ትኩረት ተሰጥቷል
ቡታጅራ፤ ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የከተሞችን የግብር አሰባሰብ አቅም በማሳደግ የመሰረተ ልማት ተደራሽነትን በራስ አቅም ለማሳካት በቅንጅት እንደሚሰራ ተገለጸ።
በክልሉ የከተሞቹን እንቅስቃሴ በማሳለጥና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን በማሳደግ ገቢያቸውን ከማሳደግ ባለፈ የማህበረሰቡን የልማት ጥያቄ በራሳቸው መፍታት እንዲችሉ ለቅንጅታዊ ሥራ ትኩረት ተሰጥቷል።
በተያዘው የ2019 በጀት ዓመትም ይህን ተግባር ለማስቀጠል አሳታፊ እቅዶችን በማውጣት ወደስራ መገባቱ ተመላክቷል።
ኢዜአ ያነጋገራችው የሆሳዕና፣ ቡታጅራ እና ወልቂጤ ከተሞች ገቢ ጽህፈት ቤቶች የሥራ ሃላፊዎች እንዳሉት በተያዘው የ2019 በጀት ዓመት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ ልማትን ለማፋጠን አቅደው ወደ ተግባር ገብተዋል።
በዚህም ለማህበረሰቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ለቅንጅታዊ አሰራርና ግብር ስወራን ለመቆጣጠር ትኩረት መስጠታቸውን ተናግረዋል።
የሆሳዕና ከተማ ገቢዎች ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አውላቸው ዮሐንስ እንደገለጹት ፤ በከተማው በበጀት ዓመቱ 4 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል።
ገቢውን ከመደበኛና ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸው በእዚህም ለማህበረሰቡ የልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች እና በደረሰኝ የሚሰበሰበው ገቢ ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን በማረም ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ ለአካባቢው ፈጣን እድገት በትኩረት እንደሚሰራም አመልክተዋል።
የቡታጅራ ከተማ ገቢዎች ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ወልዩ ከበደ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ከተማው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ የልማት ሥራዎችን በራስ አቅም ለመሸፈን ግብ ተይዞ ወደ ተግባር ተገብቷል።
በተያዘው የ2019 በጀት ዓመት በከተማው ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱንም አመልክተው፣ በተለይም በአገልግሎት ዘርፍ የሚገኝን ገቢ በማሳደግ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።
ገቢን በማሳደግ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ የታክስ ህግ የማስከበር ሥራ በቅንጅት እንደሚሰራ የተናገሩት ደግሞ የወልቂጤ ከተማ ገቢዎች ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ይድረሱ ተስፋዬ ናቸው።
እንደሃላፊው ገለጻ በበጀት ዓመቱ በከተማው 1 ቢሊዮን 77 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
የግብር አሰባሰብ ሥርአቱን ከማዘመን ባለፈ የግብር ከፋዩን ለግዢ ደረሰኝ የመስጠት ባህልን ለማሳደግና ለህግ ተገዢ እንዲሆን የማድረግ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።