ዜጎችን ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ የማድረግ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ዜጎችን ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ የማድረግ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦ በመዲናዋ ዜጎችን ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
በምናብ ያየነውን አቅደን ተግተን ፈፅመናል፤ 96 በመቶ በላይ ውጤት ማስመዝገብ ችለናል ብለዋል ከንቲባዋ በመልዕክታቸው።
ባለፉት ሶስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የነበረው የ2018 በጀት ዓመት እና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ አፈፃፀም ግምገማ በስኬት መጠናቀቁን አመልክተዋል።
በግምገማው የታቀዱ ስትራቴጂክ ግቦች በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር በተለወጠ የስራ ባህል ያለ ማቋረጥ ቀንና ማታ በመስራት በትጋት የተመዘገቡ ውጤቶችን ማላቅ እና የተለዩ ድክመቶችን በማረም በቀጣይ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ መግባባት ላይ መደረሱን አመልክተዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የአገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታላይዝ በማድረግ በተለይም ደግሞ በተያዘው በጀት ዓመት ተግባራዊ በተደረገው በመሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል የመንግስት አገልግሎት መቀየሩን ነው ያብራሩት።
ማህበራዊ ፍትህን ለማንገስ ማንንም ያልዘነጋ ህፃናት ፥ ተማሪዎች ፥ ሴቶች፥ ወጣቶች ፥ አረጋውያን ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰው ተኮር ልማቶች በትጋት መሰራቱን ነው ያመለከቱት።
2.2 ሚሊዮን የስራ ዕድል የተፈጠረበት፥ የልማቱ የጀርባ አጥንት የሆነውን የገቢ አሰባሰብ ስርዓት እጅግ ውጤታማ የነበረበት፥ ከ60 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት በተፈጸመበት፤ ከተማችን ለነዋሪዎቿ ምቹ ፣ ሀገራዊና አህጉራዊ ብሎም ዓለም አቀፋዊ ሚናዋን በብቃት የምትወጣ ፤ አዲስ አበባ ስሟና ግብሯ የተናበበ ፅዱ ፥ አረንጓዴና ውብ ከተማ የማድረግ፤ በአፍሪካ ብቻም ሳይሆን በዓለም መድረክ ጎልታ እንድትታይ አልቀን ፈፅመናል ሲሉም ገልጸዋል።
ከስኬቶቻችን ባሻገር ዛሬም ያልተሻገርናቸው ተግዳሮቶች የአመራራችን የውጤታማነት ልዩነቶች፣ የስነምግባር መጓደል፣ የመረጃ አያያዝ ክፍተቶችን ለማረም ይሰራል ብለዋል።
እንዲሁም በቀጣይ የኑሮ ውድነት እና የገበያ ማዛባትን ማስተካከል፥ የስራ እድልን ማስፋት፥ ፅዳትን ባህል ማድረግ፥ አገልግሎትን ማዘመን ፣ የመሶብ ዲጅታል አንድ ማዕከልን ማጠናከር፣ የቤት፥ ትራንስፖርት፥ መንገድ፥ ውሃ አቅርቦት ማሻሻል፥ የከተማ ማደስ በአጠቃላይ የጀመርነውን ልማት በጥራት፣ በስፋትና በፍጥነት ተጠናክሮ ይሰራል ነው ያሉት።
ጠንካራ መንግስት የመመስረት ስራም ልዩ ትኩረት የሚሰጠው እና የመረጠንን ህዝብ ይበልጥ በቅንነት ፣ በታማኝነትና በትጋት የምናገለግል መሆኑን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን ብለዋል ከንቲባዋ በመልዕክታቸው፡፡