ቀጥታ፡

በክልሉ የመሠረተ ልማት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ህብረተሰቡንና የልማት አጋሮችን በማስተባበር በተሰራው ሥራ ውጤት ተገኝቷል

ቦንጋ፤ ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦በክልሉ የመሠረተ ልማት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ህብረተሰቡንና የልማት አጋሮችን በማስተባበር በተሰራው ሥራ ውጤት መገኘቱን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።

የክልሉ የፓርቲና መንግስት የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡


 

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፣ የአመራሩን የመፈጸም አቅም በማቀናጀት በበጀት ዓመቱ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በመልካም አስተዳደር ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

የመሠረተ ልማት ተደራሽነትን ለማረጋገጥም ህብረተሰቡንና የልማት አጋሮችን በማስተባበር በተሰራው ሥራ ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ ቴክኖሎጂን ከመጠቀም ባለፈ የኩታ ገጠም አሰራርን በመተግበር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጥረት መደረጉንም አንስተዋል፡፡ 

የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የሻይና ቡና ልማትን ለማሳካት በርብርብ መሰራቱን አስታወሰው፤ በበጀት ዓመቱ 61 ሺህ ቶን የታጠበና ያልታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡንም ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር) ገልፀዋል።


 

የማዕድል ልማትን በተገቢው በመምራትም 348 ኪ.ግ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ እንደተቻለ ጠቅሰው፣ የክልሉን የውስጥ ገቢ ለማሳደግ በተደረገ ሰፊ ርብርብም ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

በመድረኩ በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት እና የክልሉ መንግስት የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2019 በጀት የዓመት ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል።

በመድረኩ የክልሉ፣  የዞኖች እና የከተማ አስተዳደር አመራሮች እየተሳተፉ ነው።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም