የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ሕግን ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጋር ያጣመረ ምክንያታዊ ጥያቄ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ሕግን ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጋር ያጣመረ ምክንያታዊ ጥያቄ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ታሪክን ከመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ሕግን ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጋር ያጣመረ ምክንያታዊ ጥያቄ መሆኑን ሊቢያዊው ምሁር ፕሮፌሰር ሳዕድ ሰላማ ገለጹ።
በኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለመታደም አዲስ አበባ የሚገኙት ሊቢያዊው ፕሮፌሰር ሳዕድ ሰላማ፤ የባሕር በር አልባ ሀገራት የባሕር ተደራሽነት በሌሎች ሀገራት በጎ ፈቃድ ብቻ ሊወሰን አይገባም ብለዋል።
ፕሮፌሰር ሳዕድ ለፐልስ ኦፍ አፍሪካ (POA) እንዳሉት፤ የባሕር በር ባለቤትነት በዘላቂ ልማትና የንግድ ትስስር የተመሠረተ መሆኑን በቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሕግጋት በግልጽ ተደንግጓል።
የባሕር በር አልባ ሀገራት ወደ ባሕር የመድረስ መብት በዓለም አቀፍ ሕግና ስምምነቶች የተረጋገጠ መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት ሀገር እንደመሆኗ፣ ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት የራሷ የባሕር በር እንደነበራት አስታውሰዋል።
የሀገሪቱ የረጅም ዘመናት የሥልጣኔ ታሪክም በቀይ ባሕር ቀጣና ከነበራት የወደብ ባለቤትነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ታሪክን ከመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ሕግን ደግሞ ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጋር አጣምሮ የያዘ ምክንያታዊ መሠረት ያለው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገሪቱ ለዚህ መብቷ ምላሽ ለማግኘት የምታደርገው ሰላማዊ የዲፕሎማሲ ጥረት በዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተረጋገጠ መሠረታዊ መብት መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ በጎረቤት ሀገራት ዘንድ በችሮታና ስጦታ የሚታይ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ሕግጋት የተመሰረተ የተፈጥሮ ሃብትን በትብብርና በጋራ የመጠቀም መብት መሆኑን አስምረውበታል።
ይህ ጥያቄ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመሥርቶ ምላሽ ካገኘም የአፍሪካ ቀንድን ሰላም፣ ንግድና የኢንቨስትመንት ትስስር በማጎልበት ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
የባሕር በር ባለቤትነት ሰላማዊና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተው ዲፕሎማሲያዊ ጥያቄና ጥረት ለቀጣናዊ ትብብርና ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ቆይታቸው የኢትዮጵያን ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ሂደትን በመታዘብ ለሀገራቸው ሊቢያ ተጨባጭ ሁኔታ የሚጠቅሙ ልምዶችን እንደሚቀስሙ ገልጸዋል።