ቀጥታ፡

በክልሉ በበጀት ዓመቱ ውጤታማ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል 

አዳማ፤ ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ ሰላምና መልካም አስተዳደርን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ውጤታማ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የሥራ ዘመን 5ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ጉባኤ በአዳማ ገልማ ጨፌ እየተካሄደ ይገኛል።


 

ፕሬዚዳንቱ የክልሉን መንግሥት የዕቅድ አፈጻጸም ባቀረቡበት ወቅት፣ በበጀት ዓመቱ ሰላምን ከማጽናትና መልካም አስተዳደርን ከማስፈን ጎን ለጎን ለልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት በ2018 ዓ.ም በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

ግብርና የኢኮኖሚ ዕድገት ዋና ምሰሶ በመሆኑ እየተከናወነ ባለው ሥራ ትላልቅ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፣ ይህም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር እየተደረገ ባለው ጥረት ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

በ2017/18 የምርት ዘመን በነበረው የመኸር ግብርና ሥራ 11 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለምቶ የተሻለ ምርት ማግኘት ተችሏል ብለዋል።

በ2018/19 የምርት ዘመን የመኸር ግብርና ልማት 12 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎች ይለማሉ ብለዋል።

እስከ አሁን ባለው ሂደትም 9 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሶ ለዘር የተዘጋጀ ሲሆን፣ 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው ደግሞ በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ተሸፍኗል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ከሻይ ቅጠል ልማት ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም የተተከሉትን ከመንከባከብ ባለፈ፣ ዘንድሮ ልማቱን ለማጠናከር በተደረገ ጥረት እስካሁን ድረስ 17 ነጥብ 9 ሚሊዮን ችግኝ መተከሉን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም ሥራው ቀጣይነት ባለው መልኩ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራም በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም እርከኖች፣ የውሃ ማስተላለፊያ መዋቅሮች፣ ልዩ ልዩ ዓይነት እርጥበትን መጠበቂያ መዋቅሮች እንዲሁም መሬትን ከሰውንና ከእንስሳት ንክኪ የመከላከል ሥራ መሠራቱን አመልክተዋል፡፡

በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በኩልም የአቮካዶ፣ የሙዝ፣ የፓፓያ፣ የአፕል እና የሌሎች የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች በስፋት መተከላቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም