በአስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ የነዋሪውን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ጥረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በአስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ የነዋሪውን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ጥረት ተደርጓል
ድሬደዋ፤ ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦ በበጀት ዓመቱ ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ የነዋሪውን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ጥረት መደረጉን የድሬደዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን ገለጸ።
የድሬደዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አብዱልሰላም መሐመድ (ዶ/ር) የተጠናቀቀውን የ2018 በጀት ዓመት የገቢ አሰባሰብና የአዲሱን በጀት ዓመት የገቢ ዕቅድ አስመልክተው ለኢዜአ ገለጻ አድርገዋል።
በመግለጫውም በአስተዳደሩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ የገቢ ምንጮችን ማስፋት ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የገቢ አሰባሰቡን ዲጂታል በማድረግና ቅንጅታዊ አሠራርን በመተግበር በበጀት ዓመቱ ከ7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አንስተዋል።
የተሰበሰበው ገቢ ከታክስና ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች መሆኑን ገልጸው፣ ይህም የዕቅዱን 78 ነጥብ 5 በመቶ ማሳካት መቻሉን ጠቁመዋል።
ገቢው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ2 ቢሊዮን 284 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው አስታውቀዋል።
የሚሰበሰበው ገቢ እየጨመረ በመምጣቱ የሕዝቡን የመሠረተ ልማት፣ የመንገድ፣ የጤና፣ የውኃና የገጠር መስኖ ጥያቄዎችን በተሻለ ፍጥነትና ጥራት ለመመለስ አስችሏል ብለዋል።
ተግባሩን አጠናክሮ በማስቀጠልም በዘንድሮው በጀት ዓመት ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።
ከከተማዋ ግብር ከፋዮች መካከል አቶ ዮሴፍ አለባቸው እንዳሉት፤ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የዘረጋው ዘመናዊ የግብር መሰብሰቢያ አሠራር ግብር ከፋዮች ኃላፊነታቸውን በወቅቱ እንዲወጡ አድርጓል።
ግብር ከፋይ ወጣት ጽዮን ተከተል በበኩሏ፤ ግብርን መክፈል ለከተማዋ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት መሠረታዊ መሆኑን በመረዳት የዜግነት ግዴታዋን መወጣቷን አንስታለች።