“ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ” ታላቁ ሩጫ በሐረር ከተማ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
“ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ” ታላቁ ሩጫ በሐረር ከተማ ተካሄደ
ሀረር ፤ ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦ “ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ 2018” የ10 ኪሎ ሜትር ታላቁ ሩጫ ውድድር በሐረር ከተማ ተካሄደ።
በውድድሩ በተለያየ የዕድሜ ክልል ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ አትሌቶች፣ ተጋባዥ እንግዶች፣ የውጪ አገር ቱሪስቶች፣ አርቲስቶችን ጨምሮ በርካታ ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ የሩጫ ውድድር ቀደም ሲል በደብረብርሃን፣ ሀዋሳ፣ ጅማ፣ አርባ ምንጭና በቆጂ ከተሞች የተካሄደ ሲሆን የፍጻሜ ውድድሩ ዛሬ በሐረር ከተማ ተካሂዷል።
በታሪካዊቷ ሐረር ከተማ በተካሄደው የታላቁ ሩጫ ውድድርን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መክዩ መሀመድና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተው አስጀምረዋል።
በ10 ኪሎ ሜትር በተካሄደው በዚህ ውድድር በወንዶች ሴና ገመቹ ሲያሸንፍ፤ ምህረት አወቀና ኢብራሂም መሀመድ በቅደም ተከተል 2ኛ እና 3ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቀዋል።
በሴቶች ራሔል እምቢበል ስታሸንፍ አምረን ሸምሱና አዚዛ መሀመድ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን አግኝተዋል።
በሁለቱም ጾታ ከተደረገው የአትሌቶች ውድድር በተጨማሪ በአዋቂዎች፣ በወጣቶች፣ በታዳጊ ሕጻናትና በሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በሁለቱም ጾታዎች የ5 ኪሎ ሜትር ውድድር ተከሂዷል።
ውድድሩን ላሸነፉ ተወዳዳሪዎች የተዘጋጀላቸውን የማበረታቻ ሽልማት ከእለቱ የክብር እንግዳ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ፣ ከባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መክዩ መሀመድ አበርክተዋል።
“ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ 2018” ታላቁ ሩጫ ውድድር ቱሪዝም ሚኒስቴር እና ታላቁ ሩጫ በኢትዮዽያ በመተባበር ያዘጋጁት የጎዳና ላይ ውድድር መሆኑ ተገልጿል።
ውድድሩ በሕዝቦች መካከል አብሮነትን የማጠናከር፣ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን የማሳደግ እንዲሁም አዲስ የስፖርት መነቃቃትን የመፍጠር ዓላማ እንዳለውም ተመላክቷል።