ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል አስተማማኝ ሰላምና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል

አዳማ፤ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል አስተማማኝ ሰላምና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

ፕሬዚዳንቱ እየተካሄደ በሚገኘው የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት የ2018 ዓ.ም የበጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ እንደተናገሩት፥የክልሉ መንግሥት ሰላምን ለማስፈንና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በወሰዳቸው እርምጃዎች ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።


 

በተለይም ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ለማድረግ በተሰራው ስራ፣ የክልሉ ህዝብ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያለውን ጽኑ ፍላጎት በተግባር ያረጋገጠበት መሆኑን ገልጸዋል።

ህዝቡ ዝናብና ፀሃይ ሳይበግረው በምርጫው በነቂስ በመሳተፍ፣ ለአፍራሽ አካላት ግልጽ መልዕክት ማስተላለፉንም ፕሬዚዳንቱ አክለዋል።

በክልሉ በተለያየ መልክ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ሙከራ ቢደረግም፤ በሰላም ወዳዱ ህዝብና በጸጥታ ኃይሎች የተቀናጀ ጥረት መክሸፉን ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።

የክልሉ መንግስት ለዘላቂ ለሰላም መስፈን ባለው ጽኑ ፍላጎት መሰረት የቀረበውን የሰላም አማራጭ በመቀበል ወደ ሰላም የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ መደበኛ ህይወታቸው መመለሳቸውን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

የመንግሥት የሰላም በር አሁንም ክፍት መሆኑን ያረጋገጡት ፕሬዚዳንቱ፤ የሰላም አማራጩን ተቀብለው ለሚመጡ ታጣቂዎች በሩ ክፍት ነው ብለዋል።

የሰላም አማራጭን ወደ ጎን በመተው በጥፋት ተግባራቸው በሚቀጥሉ አካላት ላይ የክልሉ መንግሥት ጠንካራ የህግ ማስከበር እርምጃ እንደሚወስድ አስገንዝበዋል።

በዚህም በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈንና የህግ የበላይነትን አጠናክሮ ለማስቀጠል መንግሥት በሙሉ አቅሙ እንደሚሰራም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም