ቀጥታ፡

ጨፌው በክልሉ የሰላም፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ዕቅዶች እንዲሳኩ ጠንካራ ድጋፍና ክትትል አድርጓል 

አዳማ፤ ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦ ጨፌው ባለፉት አምስት ዓመታት በክልሉ የሰላም፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ዕቅዶች እንዲሳኩ ጠንካራ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች እንዲመዘገቡ ማስቻሉን የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን ገለጹ።

የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የሥራ ዘመን 5ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በአዳማ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።


 

የጨፌው አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤ ጨፌው ባለፉት ዓመታት የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ሥራዎች በታቀደው መሠረት እንዲከናወኑ ድርሻውን ተወጥቷል።

በተለይም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ጨፌው የተጣለበትን የሕዝብ አደራ በአግባቡ ሲወጣ መቆየቱን አስታውሰው የሕዝብን ጥቅም የሚያስጠብቁ፣ ሰላም፣ ልማትና ዕድገትን የሚያፋጥኑ በርካታ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ተናግረዋል።

ሕግ በማውጣት ብቻ የታሰበውን ግብ ማሳካት ስለማይቻል፣ የወጡ ሕጎችና የልማት ዕቅዶች በተግባር ላይ እንዲውሉ ጨፌው ጠንካራ የድጋፍና የክትትል ሥራዎችን ሲያከናውን እንደነበርም አክለዋል።

በዚህም በክልሉ በሰላም፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ልማት መስኮች ተጨባጭ ስኬቶች ሊመዘገቡ መቻላቸውን ጠቁመዋል።


 

ጉባኤው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸምና ከቀጣይ አቅጣጫዎች እና በበጀት ዓመቱ በተከናወኑ የሰላምና የልማት ሥራዎች ላይ በጥልቀት በመምከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የጠቅላይ ኦዲት መስሪያ ቤት ሪፖርቶችን መርምሮ ያጸድቃል ተብሎም ይጠበቃል ብለዋል።

እንዲሁም የ2019 ዓ.ም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እቅድ ማስፈጸሚያ በጀትን ጨምሮ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት መክሮ ያጸድቃል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም