አርጀንቲና የዓለም ዋንጫ ክብሯን ታስጠብቃለች ወይስ ስፔን ከ16 ዓመታት በኋላ ዳግም አሸናፊ ትሆናለች? - ኢዜአ አማርኛ
አርጀንቲና የዓለም ዋንጫ ክብሯን ታስጠብቃለች ወይስ ስፔን ከ16 ዓመታት በኋላ ዳግም አሸናፊ ትሆናለች?
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ መርሐ ግብር ስፔን እና አርጀንቲና ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ የዓለም አይኖች አርፈውበታል።
ጨዋታው ምሽት አራት ሰዓት ላይ በኒው ዮርክ ኒው ጀርዚ ስታዲየም ይካሄዳል።
ስፔን በግማሽ ፍጻሜው ለዋንጫ ታልፋለች ተብላ የተጠበቀችውን ፈረንሳይን 2 ለ 0 በመርታት በታሪኳ ለሁለተኛ ጊዜ ለፍጻሜ ቀርባለች።
የወቅቱ የዋንጫ ባለቤት አርጀንቲና እንግሊዝን 2 ለ 1 በማሸነፍ ለተከታታይ ሁለት የዓለም ዋንጫዎች ለፍጻሜ ደርሳለች።
አርጀንቲና ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ስታልፍ የአሁኑ ለሰባተኛ ጊዜ ነው።
ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም በዓለም ዋንጫው አንድ ጊዜ ተገናኝተዋል።
እንግሊዝ እ.አ.አ በ1966 ባዘጋጀችው ስምንተኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ በምድብ ሁለት ተገናኝተው አርጀንቲና 2 ለ 1 አሸንፋለች።
ሉዊስ አርቲም ለአርጀንቲና ሁለቱን ግቦች አስቆጥሯል። ፒሪ የስፔንን ጎል በወቅቱ ያስቆጠረ ተጫዋች ነው።
ሀገራቱ በውድድር እና ወዳጅነት ጨዋታዎች 14 ጊዜ ተጫውተው በተመሳሳይ ስድስት ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ስፔን በ14ቱ ጨዋታዎች ላይ 22 ግቦችን ከመረብ ላይ ስታሳርፍ አርጀንቲና 18 ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፋለች።
እ.አ.አ በ2018 በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 19ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ስፔን ብቸኛ ክብሯን ያገኘችበት ነው።
ተጋጣሚዋ አርጀንቲና ከዚህ ቀደም ስድስት ጊዜ ለፍጻሜ ደርሳ ሶስቱን በማሸነፍ በውድድሩ ስኬታ ከሚባሉ ሀገራት መካከል አንዷ ናት።
አርጀንቲና የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈች ከጀርመን እና ጣልያን ጋር በተመሳሳይ አራት ጊዜ የዓለም ዋንጫን ያነሳች ሀገር ትሆናለች።
በተጨማሪም የደቡብ አሜሪካ ሀገር ከጣልያን እና ብራዚል በመቀጠል ዓለም ዋንጫን በተከታታይ ያነሳች ሀገር ለመሆን ትጫወታለች።
ሌላኛው ትኩረት የሳበው ጉዳይ ሀገራቱ የየአህጉራቸው ውድድሮች የወቅቱ አሸናፊ መሆናቸው ነው።
ስፔን የአውሮፓ ዋንጫ፣ አርጀንቲና የኮፓ አሜሪካ አሸናፊ ናቸው። የአውሮፓ እና የደቡብ አሜሪካ ቁንጮዎች የሚያደርጉት ፍልሚያ ትኩረትን ስቧል።
አውሮፓዊቷ ስፔን እ.አ.አ በ2010 የዓለም ዋንጫን ከማንሳቷ በፊት የ2008 የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊ ነበረች።
ስፔን የወቅቱ የአውሮፓ ዋንጫ ባለቤት ሆና ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ መቅረቧ ገጠመኙን የተለየ አድርጎታል።
በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ ድንቅ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው ሊዮኔል ሜሲ በዛሬው ጨዋታ ልዩ ትኩረት አግኝቷል።
የ39 ዓመቱ ሜሲ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ስምንት ጎሎችን በማስቆጠር እና አራት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ከኪሊያን እምባፔ (10 ጎሎች ሲያስቆጥር እና አራት የግብ እድሎችን ፈጥሯል) በኮከብ ግብ አግቢነቱ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በዓለም ዋንጫው 21 ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ በምንጊዜውም የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ዝርዝር ውስጥ በእምባፔ አንድ ጎል ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ሜሲ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ለማጠናቀቅ እና የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን መሪነት ይዞ ለመቀጠል ሁለት ግቦችን ማስቆጠር እና ለግብ የሚሆን ኳስ ማቀበል ይጠበቅበታል።
አርጀንቲናዊው ኮከብ በዓለም ዋንጫ በርካታ ጨዋታዎችን በማድረግ (33) እና በርካታ ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል (12) የክብረ ወሰን ባለቤት ነው።
እድሜው በገፋበት ሰዓት እያሳየ ያለው ብቃት አድናቆት እንዲጎርፍለት አድርጓል።
በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ አንድ ግብ ያስቆጠረው የ18 ዓመቱ ላሚን ያማል ከስፔን በኩል ትኩረት የተሰጠው ተጫዋች ነው።
ስፔን በጨዋታው ላይ የኳስ ቁጥጥርን መሰረት ያደረገ እና የክንፍ መስመር የማጥቃት እንቅሰቃሴ ላይ ያተኮረ የአጨዋወት ስልት ወደ ሜዳ ይዛ ትገባለች ተብሎ ይጠበቃል።
ተጋጣሚዋ አርጀንቲና የተደራጀ የመከላከል ቅርጽ በመያዝ ኳስ ሲያገኙ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ግብ የማስቆጠር አጨዋወትን ትከተላለች ተብሎ ይጠበቃል።
ጨዋታው ጠንካራ እና በታክቲክ የታጠረ እንደሚሆን ይጠበቃል።
የ46 ዓመቱ ስሎቬኒያዊ ስላቫኮ ቪንቺች ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
አሸናፊው ሀገር ከዋንጫው በተጨማሪ የ50 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ያገኛል። ሁለተኛ የሚወጣው ቡድን የ33 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ይበረከትለታል።
የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) አጠቃላይ በውድድሩ ላይ ለተሳተፉ ሀገራት የ871 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አዘጋጅቷል።
አሜሪካዊው ዝነኛ ድምጻዊና ራፐር ፖስት ማሎን (Post Malone) የዓለም ዋንጫው የመዝጊያ ስነ ስርዓት ዋና አቅራቢ (Headline Performer) ነው።
ከእሱ በተጨማሪ ሮቢ ዊሊያምስ፣ ኒኮል ሸርዚንገር እና ላውራ ፓውሲኒ የተባሉ ታዋቂ ድምጻውያን እንዲሁም ታዋቂው ዩቲዩበር አይሾው ስፒድ (IShowSpeed) በዝግጅቱ ላይ የሚሳተፉ ሲሆን፣ የሆሊውድ ተዋናዩ ቶም ክሩዝም ልዩ እንግዳ ሆኖ ይቀርባል።
በእረፍት ሰዓት (Halftime Show) ላይ ደግሞ ማዶና፣ ሻኪራ፣ ጀስቲን ቢበር፣ ቢቲኤስ (BTS) እና በርና ቦይ ከኮልድ ፕለይ (Coldplay) ጋር በመሆን በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚቀርበው የእረፍት ሰዓት ትዕይንት ላይ ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ።
በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ጣምራ አዘጋጅነት ከሰኔ 4 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ ሲካሄድ የቆየው 23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል።