ቀጥታ፡

እንግሊዝ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቀቅ ኪሊያን ምባፔ አዲስ የዓለም ዋንጫ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2018 (ኢዜአ)፦ 10 ጎሎች በተቆጠሩበት የ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የደረጃ ጨዋታ እንግሊዝ ፈረንሳይን 6 ለ 4 አሸንፋለች።

ከእኩለ ሌሊት በኋላ በሚያሚ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቡካዮ ሳካ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርቷል።

ሳካ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ሀትሪክ የሰራ አራተኛው ተጫዋች ሆኗል።

ዴክላን ራይስ ኢዝሪ ኮንሳ እና ጁድ ቤሊንግሃም ቀሪዎቹን ጎሎች ለሶስቱ አናብስቶች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ኪሊያን ምባፔ ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ  ብራድሊ ብራኮላ እና ኡስማን ዴምቤሌ ቀዎቹን ጎሎች ለሰማያዊዎቹ አስቆጥረዋል።

እንግሊዝ በመጀመሪያው አጋማሽ፣ ፈረንሳይ በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫ ወስደዋል።

በመጀመሪያ አጋማሽ እንግሊዝ 4 ለ 0 እየመራች ብትወጣም ፈረንሳይ ከእረፍት መልስ አራት ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፋለች።

ፈረንሳይ  ልታሻንፋባቸው የምትችልባቸውን የግብ እድሎች አምክናለች።

ጨዋታው በማጥቃት የታጀበ መሆኑንና  የቡድኖቹ የላላ የመከላከል እንቅስቃሴ በርካታ ግቦች እንዲቆጠሩ አድርጓል።

ጨዋታው አስገራሚ እንቅስቃሴ ተደርጎበታል።

የሁለቱ ቡድኖች መርሐ ግብር በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ በርካታ ግቦች የተቆጠሩበት ጨዋታ ሆኗል።

በዓለም ዋንጫ የደረጃ ጨዋታ ታሪክ በርካታ ግቦች የተቆጠሩበትም ሆኗል።

የ27 ዓመቱ ኪሊያን እምባፔ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ወደ 10 ከፍ በማድረግ የኮከብ አስቆጣሪነቱን መምራት ጀምሯል። ለግብ አመቻችቶ ያቀበላቸውን ኳሶች ብዛት አራት አድርሷል።

ከአርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ ጋር ያለውን የግብ ልዩነት ወደ ሁለት ከፍ በማድረግ የወርቅ ጫማውን የመውሰድ እድሉን አስፍቷል።

በተጨማሪም በአጠቃላይ በዓለም ዋንጫ ያስቆጠራቸውን ጎሎች 22 በማድረስ የምንጊዜም ከፍተኛ አስቆጣሪነቱን ከሜሲ (21) ተረክቧል።

ለሀገሩ 66 ጎሎችን አስቆጥሯል።

የፈረንሳዩ ማይክል ኦሊሴ በአንድ የዓለም ዋንጫ ሰባት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል የፔሌን (ስድስት የግብ እድል የመፍጠር) ክብረ ወሰንን ሰብሯል።

የ23 ዓመቱ ጁድ ቤሊንግሃም በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ሰባት ጎሎችን በማስቆጠር በውድድሩ በአንድ የዓለም ዋንጫ በርካታ ግቦችን ያስቆጠረ እንግሊዛዊ ተጫዋች ሆኗል።

ውጤቱን ተከትሎ እንግሊዝ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች።

እንግሊዝ እ.አ.አ በ1966 አዘጋጅታ ራሷ  ካስቀረችው ስምንተኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ በኋላ በውድድሩ የተሻለ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ለዋንጫ የተጠበቀችው ፈረንሳይ አራተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። 

የሁለት ጊዜ ዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ፈረንሳይ አራተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ያልተጠበቀ ሆኗል።

ለ14 ዓመት የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድንን ያሰለጠኑት የ57 ዓመቱ ዲዲየር ዴሾ የመጨረሻ ጨዋታቸውን አድርገዋል።

ዴሾ በ187 ጨዋታዎች ፈረንሳይ የመሩ ሲሆን አንድ ጊዜ የዓለም ዋንጫን አንስተዋል። ቡድኑን ለሶስት ተከታታይ ዓለም ዋንጫዎች ለፍጻሜ ያበቁ ስኬታማ አሰልጣኝም ናቸው።

ዚነዲን ዚዳን በቀጣይ ቡድኑን በአሰልጣኝነት ይረከባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም