ቀጥታ፡

ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን በትግራይ ወጣቶች ላይ እያደረሰ ያለውን አፈሳ፣ አፈናና ጭቆና ሊያቆም ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2018(ኢዜአ)፦ ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን በትግራይ ወጣቶች ላይ እያደረሰ ያለው አፈሳ፣ አፈናና ጭቆና ሊያቆም እንደሚገባ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች ገለፁ።

ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ እያካሄደ ያለውን አፈና የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ 'አፈሳ ይቁም፤ ሰላም ይስፈን' በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ተካሂዷል።


 

ተሳታፊዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በአሁኑ ወቅት ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ህገ ወጥ አስገዳጅ አዋጅ በማውጣት፣ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እና የወጣቶች ሽያጭን ጨምሮ ከፍተኛ ግፍና መከራ እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ምፅላል ገብረሃዋርያ በሰጡት አስተያየት፤ የትግራይ እናቶች ልጆቻቸው እየተገደዱ በመወሰዳቸው በከባድ ሃዘንና ስቃይ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው ህገ-ወጥ ቡድኑ ይህን ህገወጥ ድርጊት በአስቸኳይ ሊያቆም እንደሚገባ ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ወደ ተረጋጋ ሰላምና ልማት እንዲገባ፣ በአዲስ አበባና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩ የልማት ስራዎች ተጠቃሚ መሆን እንዳለባትም ተናግረዋል።

ለዚህም በተለይ የትግራይ ክልል ወጣቶች ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተፈጻሚነትና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ከፌዴራል መንግስት ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ወይዘሮ ፀሐይ ግርማ በበኩላቸው፤ ህዝቡ ፍፁም ሰላም አግኝቶ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሰርቶ መለወጥና የልማት ተጠቃሚ መሆን እንደሚፈልግ አመልክተው፤ በዚህም ከመንግስት እየቀረበ ያለውን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ የህዝቡን ሰላም ማስቀደም ይገባል ብለዋል።

ህገ-ወጡ ህወሓት በትግራይ ክልል ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለው ግፍ እና አፈና በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባ ገልጸው፤ የትግራይ ህዝብ ምርጫ ሰላምና ልማት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

አባ ናትናኤል ወልደሰንበት በሰጡት አስተያየት የፕሪቶርያው ስምምነት ከተደረገ በኋላ በትግራይ ክልል ጦርነቱ ቆሞ ሰላም ሰፍኖ ህዝቡ በነፃነት ሲሰራና ሲንቀሳቀስ እንደነበረ አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ስምምነቱን በማፍረስ የትግራይን ህዝብ ወደ ጦርነትና መከራ ለመክተት እየጣረ እንደሚገኝ ገልፀው፤ ቡድኑ ከድርጊቱ ሊቆጠብ ይገባል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ እየተካሄደ በሚገኘው አፈሳ ወጣቱ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመሰደዱ አባቶችና እናቶች ያለረዳት እየቀሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም