ቀጥታ፡

በካፋ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ከድህነት ለመውጣት ለሚደረገው ጥረት ስኬት ጥሩ ማሳያ ናቸው

ቦንጋ፤ ሐምሌ 11/2018 (ኢዜአ)፦ በካፋ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ከድህነት ለመውጣት ለሚደረገው ጥረት ስኬት ጥሩ ማሳያ መሆናቸውን የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት እና የሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደር የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ አመራሮች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማና አካባቢው የተለያዩ የልማት ስራዎችና አገልግሎት መስጫዎችን ጎብኝተዋል።


 

አመራሮቹ ከጎበኟቸው የልማት ስራዎች መካከል የእንስሳት ልማት፣ የሻይ ልማት፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና የካፋ ባህል ማዕከል ይገኙበታል።

አመራሮቹ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት በአካባቢው እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ሀገራዊ የልማት ኢንሼቲቮችን የሚደግፉና ብልፅግናን የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል የዘርፍ አስተባባሪ ሚኒስትር ዴኤታ ካሊድ አሉዋን፤ በካፋ ዞን እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች ከድህነት ለመውጣት ለሚደረገው ጥረት ስኬት ጥሩ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የውሽውሽ ሻይ ልማት ምርት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት እየቀረበ መሆኑ ከስራ እድል ፈጠራ ባለፈ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት አቅም መሆኑን አንስተው በቀጣይ ልማቱን ወደ አርሶ አደሩ የማስፋት ስራ በትኩረት እንደሚሰራበት ተናግረዋል።

መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት፣ በቦንጋ ከተማ በቅርብ ጊዜ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ መመልከታቸውን አንስተዋል።

የብልፅግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አደረጃጃት ዘርፍ ሀላፊ ጃፈር ሱፊያን እና የብልፅግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ሀላፊ መሐመድ አብዱላሒ፣ ክልሉ በተፈጥሮ ሀብት የታደለ ሰፊ የመልማት አቅም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።


 

በጉብኝታቸው በወተት ልማት የተጀመረው ስራ ተስፋ የሚሰጥና መስፋት ያለበት መሆኑን ጠቁመው አካባቢው ለእንስሳት ልማት ያለውን ምቹ ምህዳር መጠቀም እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የካፋ ባህል ማዕከል እና የአካባቢው ጥብቅ ደን ለቱሪዝም ምቹ በመሆኑ ሀብቱን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ብለዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ሰላማዊት ጠብቀው፤ የጎበኘናቸው የልማት ስራዎችና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለተጀመሩ ዘርፈ ብዙ የለውጥ ተግባራት ትልቅ ተስፋ የሰነቁ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።


 

በክልሉ ያለው እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በተቀናጀ፤ ፈጠራና ፍጥነት በታከለበት መልኩ ሰፊ ርብርብ ከተደረገበት በአጭር ጊዜ ውስጥ ብልጽግናን የማረጋገጥ ከፍተኛ አቅም እንዳለው ተመልክተናል ብለዋል።


 

አመራሮቹ በጉብኝታቸው ወቅት አረንጓዴ ዐሻራቸውንም አኑረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም