ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል የሚደረገው ህገ-ወጥ አፈና እና የሕዝብ ስቃይ ይብቃ − ምክር ቤቱ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2018(ኢዜአ) በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደሩን በማፍረስ፣ ከፌዴራል መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት በመበጠስና ህዝቡን ታጋች በማድረግ ላይ የሚገኘው ህገ-ወጡን የሕወሃት ቡድን ለማስወገድ እንደሚታገል የትግራይ የሰላምና ለውጥ ምክር ቤት ባወጣው የአቋም መግለጫ አስታወቀ።

በትግራይ የሰላምና ለውጥ ምክር ቤት አስተባባሪነት "አፈሳ ይቁም፥ ሰላም ይስፈን" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ተካሂዷል።

ሰልፉ በሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን አፈና፣ ጭቆና እና የግዳጅ ድርጊቶች ለማውገዝ የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።

የሰልፉ ተሳታፊዎች በትግራይ ክልል አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍንና ሕዝቡ የልማት ተቋዳሽ እንዲሆን ቡድኑ ህገ ወጥ ተግባራቱን እንዲያቆም ጠይቀዋል።

ቡድኑ የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት ተገን በማድረግ ስልጣን ለመጨበጥ ቢሞክርም፤እኔ የማልገዛው ህዝብ፣ የማልይዘው ስልጣን፣ የማይገባኝ መሬትና ሀብት አይኑርበሚል እኩይ እሳቤ ወርቃማውን የሰላም ዕድል ማክሸፉን ምክር ቤቱ በመግለጫው በጥብቅ ኮንኗል።

በአሁኑ ወቅት ህገ ወጡ የሕወሃት ቡድን በትግራይ ውስጥ እጅግ ጨካኝ እና ጸረ-ሰብዓዊ ህግ በማውጣት ክልሉን ወደ ምድር ሲኦል በመቀየር ሕዝቡን እያሰቃየው መሆኑም አብራርቷል።

ይኸው የጥፋት ኃይል የትግራይ ወጣቶችን በኃይል እያፈሰ ወደ ካምፕ በማስገባት፣ በኤርትራ በረሃዎች አሳልፎ ለሱዳን እየሸጣቸው መሆኑን አስታውቋል።

ይህ ለውክልና ጦርነትና ለወንጀለኞች ዕድሜ ማራዘሚያ የሚደረግ የሰዎች ሽያጭና አፈና በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባም ነው ምክር ቤቱ በመግለጫው ያሳሰበው።

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የትግራይ ህዝብ ስምምነት ስለሆነ በአግባቡ ሊተገበር ይገባል፤ ህዝባችንም የህገ ወጥ ቡድኑ ድርጊቱን እንዲያቆም የጀመረውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።

በትግራይ ክልል ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች የሚያሳትፍ፣ ሰላማዊና ለልማት የሚተጋ ስርዓት ለማምጣት ቆርጦ መነሳቱን ምክር ቤቱ ገልጾ፤ የፌዴራል መንግስት የህዝቡን ችግር ለመፍታት ለሚያደርገው ማንኛውም እንቅስቃሴ በሙሉ አቅም አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አስታውቋል።

የፌዴራል መንግስት የትግራይን ህዝብ ጥሪ ሰምቶ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ የጠየቀ ሲሆን፤ ወጣቱ የአምባገነኑን ቡድን ዕድሜ ለማሳጠር በሚደረገው ትግል በጋራ እንዲሰለፍ በአቋም መግለጫው ጥሪ አቅርቧል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #ENA

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም