ቀጥታ፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ከመቋቋም ባለፈ የወጣቶችን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ባህል አሳድጓል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2018(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ከመቋቋም ባለፈ የወጣቶችን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ባህል እያሳደገ መሆኑን የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ገለጸ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር የደን መመናመንና የአፈር መሸርሸርን በመከላከል በኩል አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።


 

ባለፉት ዓመታት ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን በዘንድሮው ዓመትም 'ተስፋን እንትከል' በሚል መሪ ሐሳብ ከ8 ቢሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ወደ ትግበራ ተገብቷል፡፡

መርሃግብሩ የሀገሪቱን የደንና የአረንጓዴ ሽፋን ከማሳደጉ ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር አስችሏል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ከከተማ አስተዳደሩ የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር በዛሬው ዕለት አካሂዷል።

በመርሃ-ግብሩ የተሳተፉ ኃላፊዎችና ወጣቶች የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ፣ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ባህልን ለማሳደግ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ፎሊ ንጉሴ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም፣ የከተማዋን ውበት ለመጠበቅና ምቹ አካባቢን ለመፍጠር አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግራለች።

ችግኝ ከመትከል ባለፈ በዘላቂነት መንከባከብና መጠበቅ እንደሚገባም ገልፃለች።

የማህበሩ ዋና ጸሐፊ ኤርሚያስ ወንድሙ በበኩሉ፣ የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተበሰረበት ጊዜ አንስቶ ወጣቱ በንቃት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ተናግሯል።


 

መርሃ-ግብሩ ለተተኪው ትውልድ የተሻለች፣ በልምላሜና በተስፋ የተሞላች ሀገር ማስረከብ የሚያስችል መሆኑንም ገልጿል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ከተማዋን አረንጓዴ፣ ፅዱና ምቹ ስነ-ምህዳር እንድትላበስ አስችሏል ያሉት ደግሞ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ የጽዳትና ውበት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የኑስ መሐመድ ናቸው።


 

በመርሃግብሩ የተሳተፉት ወጣት ከተማ ባልቻና ወጣት ተገኑ ቦነ በበኩላቸው ዛሬ ችግኞችን መንከባከብ ለመጪው ትውልድ ዐሻራን ማኖር በመሆኑ ችግኞችን በዘላቂነት እንደሚንከባከቡ ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም