ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና ስጋቶችን ቀድሞ በመከላከል አቅም ገንብቶ በማየታችን ኮርተናል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የሕብረተሰብ ጤና ስጋቶችን መከላከልና ለወረርሽኞች የተቀናጀና ሳይንሳዊ ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም በመገንባቱ ኩራት እንደተሰማቸው ተቋሙን ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ሠራተኞችና የቀድሞ አመራር ገለጹ።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ100ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ኹነቶች ያከበረ ሲሆን፣ ተቋሙን ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ አመራሮችና ሠራተኞች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።


 

እውቅና ከተሰጣቸው መካከል ተቋሙን ለ25 ዓመታት ከተመራማሪነት እስከ ዋና ዳይሬክተርነት ያገለገሉት ዶክተር አምሃ ከበደ አንዱ ናቸው።

የቀድሞው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አምሃ በተለያየ የሙያና የኃላፊነት እርከን በማገልገል የተቋሙ የምዕተ ዓመት ታሪክ ላይ አስተዋፅኦ ማበርከታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ዓመታት ባካሄዳቸው መዋቅራዊ ሪፎርሞች ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የሕብረተሰብ ጤና ስጋቶችን ቀድሞ የመከላከል አቅሙን በማሳደጉ ኩራት እንደተሰማቸው ገልፀዋል።

ኮቪድ-19ን ጨምሮ በቅርቡ የተከሰቱትን ኤምፖክስና ማርበርግ የመሰሉ ወረርሽኞችን በተቀናጀ፣ ፈጣንና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመመከት በኩል ያስመዘገበው ስኬት ተቋሙ የደረሰበት የላቀ የመከላከል አቅም ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

በተቋሙ ለ44 ዓመታት በማገልገል የሕይወት ዘመን ተሸላሚ የሆኑት ጎንፋ አያና ተቋሙን ባገለገሉባቸው ዓመታት ኢንስቲትዩቱ የስምና አደረጃጀት ለውጥ በማድረግ በሕብረተሰብ ጤና ላይ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ አሁን ላይ የቴክኖሎጂና የባለሙያ አቅሙን በማሳደግ ተወዳዳሪ ተቋም መሆን መቻሉን ተናግረዋል።

ለበርካታ ዓመታት በማገልገል እውቅና በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸው፣ የአሁኑ ትውልድም ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ሀገሩን በተሻለ መንገድ እንዲያገለግል አስገንዝበዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #ENA

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም