በምሥራቅ ቦረና ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ61 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በምሥራቅ ቦረና ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ61 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል
ነገሌ ቦረና፣ ሐምሌ 11/2018 (ኢዜአ)፦ በምሥራቅ ቦረና ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ61 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የዞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የጽሕፈት ቤቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ቡድን መሪ አቶ ጎዳና ሳራ እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ለ53 ሺህ 266 ወጣቶች የሥራ ዕድል ለማመቻቸት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
በተሠራው ሥራም በዕቅድ ከተቀመጠው በላይ 61 ሺህ 111 ወጣቶችን በተለያዩ አራት ዋና ዋና የሥራ ዘርፎች ማሰማራት ተችሏል ብለዋል።
እነዚህ ወጣቶች በ121 የኅብረት ሥራ ማኅበራት ተደራጅተው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል 21 ሺህ 997ቱ ሴቶች ሲሆኑ፣ ከ6 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህ የተመቻቸው የሥራ ዕድል የአርብቶ አደሩን የሥራ ባሕል በማጎልበትና በራስ አቅም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
የእንስሳት እርባታና ማድለብ፣ የአትክልትና ሥራሥር እንዲሁም የመስኖ ልማት፣ የማዕድን ልማት፣ የግብይትና ንግድ ሥራዎች፣ እና የእንጨትና ብረታብረት ውጤቶች ማምረት የሥራ ዕድሉ የተፈጠረባቸው ዘርፎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የጽሕፈት ቤቱ የፋይናንስ አቅርቦት ባለሙያ አቶ ቦሩ ገልገሎ በበኩላቸው፤ ለበጀት ዓመቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ማስፈጸሚያ የሚሆን 464 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የብድር አቅርቦት ታቅዶ እንደነበር አስታውሰዋል።
በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከ578 ሚሊዮን 943 ሺህ ብር በላይ ብድር ማሰራጨት እንደተቻለም አመልክተዋል።
ከፋይናንስ አቅርቦቱ በተጨማሪም በገጠር ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ የማምረቻ ቦታ፣ በከተሞች ደግሞ 150 የመሸጫ ሼዶች ለተጠቃሚዎቹ ድጋፍ መደረጉን ባለሙያው ጠቅሰዋል።
የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪው ወጣት ቢኒያም አምሳሉ፤ በእንጨትና ብረታብረት ሥራ መስክ ከሁለት ባልደረቦቹ ጋር በመደራጀት የቤትና የቢሮ ዕቃዎችን እያመረቱ መሆኑን ተናግሯል።
የተደረገላቸው የማምረቻ ቦታና የብድር አገልግሎት ድጋፍ ሠርቶ ለመለወጥ ትልቅ አቅምና መነሳሳት እንደፈጠረላቸውም ገልጿል።
በተመሳሳይ በእንጨት ሥራ ዘርፍ የተሰማራው ወጣት አብዲ ሁሴን በበኩሉ፤ ከሦስት ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ሥራ ሳይንቁና ሳይመርጡ በቁርጠኝነት በመሥራት ሕይወታቸውን እያሻሻሉ እንደሚገኙ ገልጿል።
የተመቻቸላቸው የብድር አገልግሎት ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከመደገፍ ባለፈ፣ ወደፊት ሌሎችንም ለመርዳት አቅደው እንዲሰሩ በር እንደከፈተላቸው አክሏል።