ቀጥታ፡

በከተማዋ የሚገነቡ መሰረተ ልማቶችን በመጠበቅ ረገድ ውጤታማ የደንብ ማስከበር ስራ ተከናውኗል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2018(ኢዜአ)፦ በከተማዋ የሚገነቡ መሰረተ ልማቶችን በመጠበቅ ረገድ ውጤታማ የደንብ ማስከበር ስራ መከናወኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ገለጹ፡፡  

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት ማጠቃለያ የስራ አፈጻጸም ግምገማ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ፤ አዲስ አበባ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገች እና እየተለወጠች በመምጣቷ ለነዋሪዎቿ ምቹ መሆኗን ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ የመሰረተ ልማቶችን የመጠበቅ፣ የመሬት ወረራን የመከላከል፣ ህገ-ወጥ ግንባታን የመከታተል፣ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቶችን የመቆጣጠር፣ ህገ-ወጥ ንግድን የመከላከል እና ሌሎች ተጨማሪ ተልዕኮዎችን ወስዶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 

በበጀት ዓመቱ በከተማዋ የሚገነቡ መሰረተ ልማቶችን በመጠበቅ ረገድ ውጤታማ የደንብ ማስከበር ስራ መከናወኑን ጠቁመው፣ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀትም ከተማዋ ውብ እና ጽዱ እንድትሆን ያስቻሉ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወናቸውን ተናግረዋል።

የመሬት ወረራን በመከላከል እና ህገ-ወጥ ግንባታዎችን በመቆጣጠር ረገድ ስኬታማ ስራ መከናወኑን ጠቁመው፣ ህገ-ወጥ ንግድን በመከላከል ረገድ በተከናወኑ ስራዎችም የከተማዋ ጎዳናዎች ከህገ-ወጥ ንግድ ነጻ መደረጋቸውን አመልክተዋል። 

ባለስልጣኑ ዲጂታል የቴክኖሎጂ ስርዓቶችን በመጠቀም የቁጥጥር ስርዓቱን ውጤታማ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው፣ የደንብ ጥሰቶች ይፈጸሙባቸዋል ተብለው በሚታሰቡ አካባቢዎች ካሜራዎችን በመግጠም ከሲቹዌሽን ሩም በመሆን የዕለት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ህይወት ሳሙኤል የከተማዋን ስታንዳርድ ከማስጠበቅ ረገድ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል። 

በዚህም በከተማዋ ወጥ የሆነ የቀለም ስታንዳርድ መውጣቱን ተናግረው፣ በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ዙሪያም በየአመቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ አልሚዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት አምስት አመታት አዲስ አበባ በመዋቅራዊ ፕላኗ ብቻ እንድትመራ መደረጉን ጠቁመው፣ ህገ-ወጥ ግንባታዎች እንዲቀሩ በተከናወኑ ስራዎች አበረታች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

የማስታወቂያ ቦርዶችን ዲጂታል ለማድረግ የተከናወኑ ስራዎች ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት መፍጠራቸውን ገልጸዋል። 

በቀጣዮቹ ጊዜያትም የህብረተሰቡን እርካታ ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ እና ልማቱን ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም