ቀጥታ፡

በዞኑ የተገነቡና የተሻሻሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ዘላቂ ተጠቃሚነታችንን አሳድጎታል

ገንዳውኃ፣ ሐምሌ11/2018(ኢዜአ)፡-በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተገነቡና የተሻሻሉ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ለረዥም ጊዜ በውሃ እጥረት ሳቢያ ሲደርስባቸው የነበረውን እንግልት እንዳስቀረላቸው የምዕራብ ጎንደር ዞን ነዋሪዎች ገለጹ። 

​ከ193 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ አዲስ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ መካሄዱን የዞኑ ውሃ እና ኢነርጂ መምሪያ አስታውቋል። 

በዞኑ መተማ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ፋሲካ ሲሳይ፣ በአካባቢያቸው የውሃ ተቋማት ተገንብቶ ተጠቃሚ መሆናቸው  የመጠጥ ውሃ ለማግኝት ይጓዙ የነበረውን ረጅም ርቀት በማስቀረት እፎይታን እንደሰጣቸው ይናገራሉ። 

 በተለይም ሴቶችና ህጻናት የመጠጥ ውሃ ለማግኝት ይደርስብን የነበረውን እንግልት ከማስቀረቱ  ባሻገር ከውሃ ወለድ በሽታ እንድንጠበቅ አድርጎል ነው የሚሉት።

በወረዳው የኮኪት ከተማ ነዋሪ አቶ ሙሃመድ አሊ በበኩላቸው፣ የመጠጥ ውሃ ተቋማቱ  መገንባት እናቶችና ሕፃናት  ውሃ ለመቅዳት የሚጠበቅባቸውን ረዥም ሰአት  ለልማት ስራ እንዲያውሉት የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል። 

በተለይም በፀኃይ ብርሃን የሚሰሩ የውሃ ተቋማት መገንባታቸው በነዳጅ እጥረትና በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ሳቢያ ሲስተጓጎል የነበረውን የውሃ አቅርቦት ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ብለዋል።

​የምዕራብ ጎንደር ዞን ውሃና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ይርዳው ካሳው በበኩላቸው፤ የተከናወኑት የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታዎች የሕዝቡን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት ያስቻሉ እንደሆነም ነው የተናገሩት ። 

​በበጀት ዓመቱም ከ193 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ  የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ መካሄዱን ነው  የገለጹት። 

ከዚህ ውስጥም ከ115 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 31 አዳዲስ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል ነው ያሉት። 

በተጨማሪም ከ78 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሰባት ነባር የውሃ ተቋማት በፀሃይ ብርሃን እንዲሰሩ መደረጉንም አስገንዝበዋል።

ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁት የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ከ30 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ መሆናቸውን አንስተዋል።

​የውሃ ተቋማቱን የአገልግሎት ጊዜ ለማራዘም ማህበረሰብ ጥበቃና እንክብካቤ ሊያደርግላቸው እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም