ቀጥታ፡

በዞኑ ከሁለት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአትክልት እና ፍራፍሬ ተሸፍኗል

ነቀምቴ፣ሐምሌ 11/2018 (ኢዜአ)፡-በምስራቅ ወለጋ ዞን ከ ሁለት ሺህ  ሄክታር በላይ መሬት በአትክልት እና ፍራፍሬ መሸፈኑን የዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

የምስራቅ ወለጋ ዞን የአትክልት እና ፍራፍሬ ባለሙያ አቶ ታከለ መኮንን  ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ በአትክልት እና ፍራፍሬ ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ ነው።

በተለይ  በአቮካዶ፣ ሙዝ፣ ማንጎ ፣ እና ፓፓያ  ምርት ላይ ትኩረት ተደርጎ በመሰራቱ ውጤት ያስገኘ በመሆኑ አርሶ አደሩን ይበልጥ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል። 

ለአብነትም በ2018 የምርት ዘመን 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል በላይ  የተለያዩ ፍራፍሬዎችን ለማምረት ታቅዶ ከእቅድ በላይ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን  ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ተችሏል ነው ያሉት ።

በዘንድሮው አመት በክላስተር እና በመደበኛ ከሁለት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በላይ በፍራፍሬ እና አትክልት መሸፈን መቻሉን ገልጸዋል።

በዞኑ በፍራፍሬ  እና በአትክልት ልማቱ  ስራ ላይም 580 ሺህ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

የምስራቅ ወለጋ ዞን ጉቶ ጊዳ ወረዳ አርሶ አደር ገለታ ውሉ ፤ላለፉት ሶስት አመታት በአቮካዶ ምርት ላይ  በመሳተፍና የባለሙያዎችን መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እንዳስቻላቸው ይገልፃሉ።

በሁለት ሔክታር መሬት ላይ በክላስተር  አቮካዶን በማልማትም የተሻለ ምርት ለገበያ ለማቅረብ እየሰሩ መሆኑን ነው የሚገልጹት።

ሌላኛው አርሶ አደር አቶ ታሪኩ ነጋሳ በክላስተር የተለያዩ ፍራፍሬዎችን እያመረቱ እንደሚገኙ ገልፀው በዚህም ከራሳቸው አልፈው ለአካባቢው አምራች አርሶ አደር ልምድ እያካፈሉ መሆኑን ገልጸዋል።
ምርቱም ከምግብ በዘለለ በገቢ ምንጭነት እየተጠቀሙበት መሆኑን ነው የሚገልጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም