ቀጥታ፡

የዲጂታል ሪፎርሙ በአዲስ አበባ የመሬት ዘርፍ ብልሹ አሰራርን በመቀነስ ገቢን አሳድጓል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የተተገበረው የዲጂታል ሪፎርም የመሬት አገልግሎትን በማዘመን፣ ብልሹ አሰራርን በመቀነስና የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን በማጠናከር ውጤታማ ለውጥ ማምጣቱን የከተማው መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ኃላፊ መኮንን ያኢ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ሪፎርም ተከትሎ በከተማው የመሬት አገልግሎትን ዘመናዊ፣ ግልጽና ከሰው ንክኪ የተላቀቀ ለማድረግ ሰፊ የለውጥ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በሪፎርሙ ማዕቀፍ ከ720 ሺህ በላይ የመሬት ማህደራት ስካን ተደርገው ወደ ዲጂታል መረጃ ቋት መግባታቸውን ገልጸው፤ የመረጃ ደህንነትን ከማጠናከር ባለፈ ህገ ወጥ የካርታ ዝግጅትና የመሬት ወረራ ወንጀሎችን ለመቀነስ አስተዋፅኦ አበርክቷል ብለዋል።

በተጨማሪም የመሬት አገልግሎቶችን በኦንላይን ስርዓት በማቅረብ የአገልግሎት ፍጥነትን ከማሳደግ በተጨማሪ ለሙስናና ብልሹ አሰራር የነበረውን ተጋላጭነት በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን ገልጸዋል።

በዘጠኝ ወራት ውስጥ 39 ሺህ የሚጠጉ ኢ-ካርታዎች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው፤ የይዞታ መረጃዎችም በዲጂታል ስርዓት እንዲመዘገቡና እንዲጠበቁ መደረጉን አመልክተዋል።

በአስራ አንዱ ክፍለ ከተሞች ተበታትኖ የነበረውን የመሬት ቤዝማፕ ወደ አንድ ማዕከላዊ የመረጃ ቋት ማምጣት መቻሉንም ጨምረው አብራርተዋል።

አቶ መኮንን እንዳሉት፤ ቢሮው በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዘ የተቀናጀ የመሬት መረጃ ስርዓት ወደ ስራ በማስገባት የሁለተኛ የመብት ፈጠራ፣ የካርታ ድርርቦሽና ሌሎች የማጭበርበር ሙከራዎችን ከመፈጸማቸው በፊት የሚለይና ለባለይዞታዎች ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ የቴክኖሎጂ አቅም ገንብቷል።

በአዲስ መሶብ አገልግሎት ማዕከላት 14 የመሬት አገልግሎቶችን ወደ ዘመናዊ የአንድ ማዕከል ስርዓት በማስገባት በቀጣዮቹ 90 ቀናት በአስራ አንዱም ማዕከላት ሙሉ በሙሉ እንዲሰጡ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አሰራሩ የአገልግሎት መዘግየትን በመቀነስ ሙስናን ለመግታት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት አመልክተዋል።

የመሬት አገልግሎት ዲጂታላይዜሽን በገቢ አሰባሰብ ላይም ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን ጠቁመው፤ ከአምስት ዓመታት በፊት ከአምስት ቢሊየን ብር ያልበለጠ የነበረው ከመሬትና ይዞታ የሚገኝ ገቢ በ2018 በጀት ዓመት 19 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መድረሱን ተናግረዋል።

በመሬት ዘርፉ የሚፈጸሙ ህገ ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከልና ተጠያቂነትን ለማስፈን በርካታ አመራሮችና ሰራተኞች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ገልጸው፤ ይህም አገልግሎቱን ግልጽ፣ ተጠያቂና ለተገልጋዮች አስተማማኝ ለማድረግ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም