ቀጥታ፡

ባለፉት አምስት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ በመንገድና በውሃ መሰረተ ልማት ዘርፍ አስደናቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2018(ኢዜአ)፦ ባለፉት አምስት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ በመንገድና በውሃ መሰረተ ልማት ዘርፍ አስደናቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን እና ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት የሥራ ሃላፊዎች ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሙህዲን ረሻድ እንደገለጹት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት የትራንስፖርት ፍሰትን ለማሻሻልና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።


 

በዚህ ጊዜ ውስጥ የከተማዋ የመንገድ ሽፋን 8 ሺህ 227 በላይ ኪሎ ሜትር መድረሱንና በተጀመረው አዲሱ በጀት ዓመትም 1ሺህ 600 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመንገድ ግንባታና ጥገና ለማከናወን ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።

እነዚህ መንገዶች የትራንስፖርት ፍሰትን ከማሳለጥ ባለፈ ለህብረተሰቡ ያላቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ የጎላ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት 1ሺህ 300 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት ታቅዶ 1ሺህ 600 ኪሎ ሜትር መከናወኑን በማስታወስ፣ ትልቅ የመልካም አስተዳደር ችግር የነበራቸው ፕሮጀክቶች መፍትሄ ማግኘታቸውን አብራርተዋል።

ስራዎቹ የከተማዋን የመንገድ መሰረተ ልማት በማዘመን የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተተገበሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡


 

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዘርሁን አባተ በበኩላቸው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ከውሃ አቅርቦት እና የፍሳሽ መሰረተ ልማት ላይ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል።

ለአብነትም ውሃ የማምረት አቅምን ወደ 850 ሺህ ሜትር ኪዩብ ማደረስ መቻሉን ጠቅሰው ይህን አቅም ማሳዳግ የተቻለው 150 የሚደርሱ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች በመቆፈር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከፍሳሽ መሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ ከ1ሺህ 500 ኪሎ ሜትር በላይ የፍሳሽ መስመር መዘርጋቱን ጠቁመው ትላልቅ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም